ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ የንግድ ግንኙነታቸውን በይበልጥ ለማጠናከር ተስማሙ

You are currently viewing ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ የንግድ ግንኙነታቸውን በይበልጥ ለማጠናከር ተስማሙ

AMN ጥቅምት 24/2018

ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ የንግድ ግንኙነታቸውን በይበልጥ ለማስፋትና ለማጠናከር መስማማታቸው ተገለጹ።

የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ከፈረንሣይ የውጭ ንግድና ኢኮኖሚ ሚኒስትር ተወካይ ኒኮላስ ፎሪሲየር ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል።

በውይይታቸውም፤ የሁለትዮሽ የኢኮኖሚ ትብብርን በይበልጥ ማሳደግ እና በኢትዮጵያ ተጨማሪ የፈረንሳይ ኢንቨስትመንትን ማበረታታት በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ መክረዋል።

በዚህም መሠረት ሀገራቱ በዘላቂና ሁሉን አቀፍ ዕድገት ላይ የነበራቸውን ትብብር ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆናቸው ተገልጿል።

ለአብነትም፤ በኢንዱስትሪ ልማት፣ ታዳሽ ኃይል፣ መሠረተ-ልማት፣ የግብርና ማቀነባበሪያ፣ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች በትብብር የሚከናወኑ ተግባራት መኖራቸው ተጠቁሟል።

አቶ አሕመድ በውይይቱ ወቅት ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ የልማት ተነሳሽነት ላደረገችውና እያደረገች ላለው ቀጣይነት ያለው ድጋፍ አመሥግነዋል።

ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፉን በይበልጥ ለማሻሻል እየሠራች መሆኗን ጠቁመው፤ ለአብነትም ፖሊሲን ጨምሮ ተቋማዊ ሪፎርሞች ማድረጓን አስታውቀዋል።

ይህም በዘርፉ በይበልጥ ቀጣይነት ያለው ዓለም አቀፍ ተሳትፎን ከማሳደግ ባለፈ ቀልጣፋና ምቹ አገልግሎት ለማግኘት ማስቻሉን ነው ያስረዱት።

የኢትዮጵያን ዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካት የኢኮኖሚ ትስስሩን ማስፋትና ማጠናከር እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።

ኒኮላስ ፎሪሲየር በበኩላቸው የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ አድንቀው፤ ፈረንሳይ በቀጣይም የንግድ ትስስሩን ለማስፋት፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ብሎም የኢንቨስትመንት ትብብርን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ማረጋገጣቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በፈረንጆቹ ግንቦት 2026 የፈረንሣይ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ በሚያደርገው ይፋዊ ጉብኝት ሁለቱም ወገኖች ውይይቱን ለመቀጠል መስማማታቸው ተመላክቷል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review