የሽንት ኢንፌክሽን ህመም በሽንት መስመር ውስጥ ጀርሞች በመግባት የሚፈጥሩት እክል ስለመሆኑ በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የዩሮሎጂ ሰብ ስፔሻላይዝድ ሐኪም ዶክተር አሕመድ አበበ ይገልፃሉ፡፡
ዶክተር አሕመድ ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የሽንት ኢንፌክሽን ህመም እና መከላከያ መንገዱን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ በማብራሪያቸውም የሰውነት አካል አሰራር በራሱ ለሽንት ኢንፌክሽን የሚያጋልጡ ምክንያቶች እንዳሉት ተናግረዋል፡፡
በተለይ የሴቶች ከሽንት ፊኛ እስከ ሽንት መውጫ ያለው አጭር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ባክቴሪያዎች በቀላሉ ወደ ሽንት ፊኛ ሊገቡ ይችላሉ ያሉ ሲሆን፣ ይህም አንዱ የተጋላጭነት መንስኤ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሁለተኛው ዕድሜ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር አሕመድ፣ ህፃናት የሰውነታቸው የመከላከል አቅም ገና ያልዳበረ፣ የትልልቆቹ ደግሞ የደከመ በመሆኑ በቀላሉ ለሽንት ኢንፌክሽን ሊጋለጡ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡
ሌላው የሽንት መስመር ላይ የተፈጠረ ሌላ እክል ሲያጋጥም ሊጸጠር የሚችል ሲሆን ፤ በጠጠር ወይም ወንዶች ላይ የፕሮስቴት እብጠት ካለ የሽንት መስመር መዘጋት ይኖራል ይህ ደግሞ ለባክቴሪያዎች በቀላሉ እንዲራቡና እንዲዛመቱ ምኡ እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡
የመጀመሪያው የሽንት ኢንፌክሽን ለመከላከል የሚጠቅመው ዘዴ ብዙ ውሃ መጠጣት ነው።
አንድ ወጣት ወይም ትልቅ ሰው በ24 ሰዓታት ውስጥ ከ6 እስከ 8 ብርጭቆ ወይም ከሁለት ሊትር በላይ ውሃ እንዲጠቀም እንደሚመከርም ጠቁመዋል፡፡
ሁለተኛ የሽንት መውጫ ጫፍ ላይ እርጥበት እና ሙቀት ካለ ባክቴሪያዎች በቀላሉ የመራባት እና ወደ ሽንት ቱቦ የመግባት ዕድል እንደሚኖራቸው ያነሱት ባለሙያው፣ የሽንት መውጫ ጫፍ አካባቢን ከእርጥበት እና ከሙቀት መቀነስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በተለይ ለሴቶች ከተጸዳዱ በኋላ መታጠብም ይሁን በሶፍት ማፅዳት፣ ከሰገራ አቅጣጫ ወደ ሽንት ቱቦ አቅጣጫ ሳይሆን ወደ ኋላ ማፅዳት እንደሚመከር አመላክተዋል፡፡

ካፊን የበዛባቸው መጠጦች ብዙውን ጊዜ የምንጠቀም ከሆነ የሽንት ፊኛ መቆጣት ስለሚፈጠር በቀላሉ ባክቴሪያዎችን የመያዝ አቅም ሊኖረው እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡
አልኮል መጠጣት፣ የአለባበስ ሁኔታ፣ ሽንት መውጫ አካባቢ እርጥበትና ሙቀት እንዳይኖር ከጥጥ የተሰሩ የውስጥ ልብሶችን መጠቀም የተሻለ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
አንድ ሰው ሽንት የመምጣት ስሜት ካለው ወዲያው እንዲሸና ይመከራል ያሉት ዶክተር አሕመድ፣ ይህም ሽንቱ በሚቆይበት ሰዓት ባክቴሪያዎችን የማከማቸት ነገር ሊፈጥር ስለሚችል ይህን ለማስወገድ እንደሚጠቅም አስረድተዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ ሽንት በሚሸናበት ጊዜ በሽንት መስመር ላይ የነበሩ ባክቴሪያዎችን ጠርጎ ለማውጣት ዕድል ስላለው፣ ማንኛውም ሰው ሽንት በሚመጣበት ጊዜ ወዲያው እንዲሸና ይመከራል ብለዋል፡፡
ብዙ ጊዜ ሰዎች የሽንት ኢንፌክሽን እየተባለ የተለያዩ መድሃኒቶች እንደሚወስዱ የተናገሩት ባለሙያው፣ መድሃኒቶችን ያለ ሐኪም ትዕዛዝ መውሰድም ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም በተደጋጋሚ የሽንት ኢንፌክሽን ከተባለ፣ የዩሮሎጂ ስፔሻሊስቶች ጋር መሄድ እንደሚመከር በአፅንኦት አስገንዝበዋል፡፡
በታምራት ቢሻው