ተጠርጣሪዎቹ በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች በመንቀሳቀስ ያልታመመ ሰው ታማሚ አስመስለው እና ተሽከርካሪ ውስጥ አስተኝተው ሃሰተኛ ሰነድ በመጠቀም ከህብረተሰቡ ገንዘብ ሲሰበስቡ ተገኝተው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል፡፡
አንድን ወጣት የኩላሊት ታማሚ በማስመሰል በተከራዩት የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3- 26734 ኦሮ የሆነ ሚኒባስ ውስጥ አስተኝተው በእርዳታ ስም ከህብረተሰቡ ገንዘብ ሲሰበስቡ የነበሩት እነዚህ ተጠርጣሪዎች ሊያዙ የቻሉት አያት አደባባይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ባደረገው ክትትል ነው።

በተሽከርካሪው ውስጥ በተደረገ ፍተሻ በዕርዳታ ስም የተሰበሰበ 23 ሺህ 325 ብር የተገኘ ሲሆን በተጨማሪም በሃሰት የተዘጋጀ የህክምና ሰነድ እንዲሁም የድጋፍ ደብዳቤ እንደተገኘ እና በሰነዶቹ ላይ ፖሊስ ባደረገው ማጣራት ሃሰተኛ መሆናቸው እንደተረጋገጠ ተገልጿል፡፡
ገንዘብ በመሰብሰብ ስራ ላይ ለተሰማሩት ግለሰቦች በቀን 300 ብር የሚከፈላቸው ሲሆን ተሽከርካሪውን በቀን 3000 ሺህ ብር እንደተከራዩት እና ለአሽከርካሪው አንድ ሺህ ብር እንደሚከፈለውም ተረጋግጧል።
በወንጀሉ በቀጥታ የተሳተፉ እና የተባበሩ በአጠቃላይ 9 ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝ የጠቀሰው የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ፤ በየመንገዱ የሚካሄዱ እንዲህ አይነት ህገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከል ህብረተሰቡ ድጋፍ ማድረግ በሚፈልግበት ወቅት ተገቢውን ማጣራት እንዲያደርግ እና አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ለሚመለከተው አካል ጥቆማ እንዲሰጥ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ ጥሪውን አቅርቧል፡፡