በአጭር ጊዜ ከተማን መለወጥ እንደሚቻል አዲስ አበባ ማሳያ ናት

You are currently viewing በአጭር ጊዜ ከተማን መለወጥ እንደሚቻል አዲስ አበባ ማሳያ ናት

AMN – ጥቅምት 25/2018 ዓ.ም

ጠንካራ አመራር ካለ በአጭር ጊዜ ከተማን መለወጥ እንደሚቻል አዲስ አበባ ማሳያ ናት ሲሉ ከቡርኪናፋሶ የመጡ የልዑካን ቡድን አባላት ተናግረዋል፡፡‎

የልዑካን ቡድኑ በአዲስ አበባ ከተማ የተሰሩ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ገብኝተዋል፡፡

አዲስ አበባ መሰረተ ልማቶቿ፣ ንጹህ ጐዳናዎቿ እና አስደናቂ የልማት ኘሮጀክቶቿ ከአፍሪካ ውብና ዘመናዊ ከተሞች አንዷ እንድትሆን ያደረጋት ሲሆን በዚህም የብዙ አፍሪካዊያንን ትኩረት እንድትስብ አድርጓታል፡፡

ጉብኝቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር፣ ኢትዮጵያ በከተማ ኘላን፣ በትራንስፖርት ሥርዓትና በአካባቢ አያያዝ እያስመዘገበች ያለችውን እድገት ልምድ ለመቅሰም ያለመ ነው ተብሏል፡፡

የቡርኪናፋሶ ኘሬዝደንት አማካሪ ዣቤል ትራኦሬ አዲስ አበባ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጥሩ ምሳሌ መሆን የምትችል ከተማ መሆኗን ገልፀው፤ይህ ለውጥ የመጣው ጠንካራ አመራር፣ ህልም እና ትጋት በመኖሩ ነው ብለዋል፡፡

አዲስ አበባን አስደናቂ፣ ሳቢ፣ ዘመናዊ አገልግሎት የሚሰጥባት፣ በፍጥነት ያደገች እና ጥሩ መሠረተ ልማት ያላት ከተማ መሆኗን በጉብኝቱ አረጋግጫለሁ ነው ያሉት፡:

ፍላጎትና ተነሳሽነት ካለ የማይሳካ ነገር እንደማይኖር አዲስ አበባ ጥሩ ምሳሌ ናት ሲሉም ገልፀዋል፡፡

ሌላው የቡድኑ አባላት ጋይታ ዊድራውጎ እንዳሉት የተሰሩ የልማት ሥራዎች አዲስ አበባ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አበረታች ምሳሌ እንድትሆን አስችሏታል። ይህም የአፍሪካን አንድነትና ቀጣይነት ያለው ተጠቃሚነት የጎላ እንዲሆን ያስችለዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ቡርኪናፋሶ በኘሬዚዳንት ኢብራሂም ትራኦሬ በተለይ በወጣት መሪ ልታሳካ ያለመችው በመሰረተ ልማት፣ በምግብ፣ በጤናና በግብርና መስክ ሁሉ ራሷን ማሳደግ ነው ብለዋል፡፡

በጥቂት አመታትም በቡርኪናፋሶ ለውጥ እንዲመጣ ነው እየተሰራ ያለው ለዚያም ነው በፍጥነት ለውጥ እንዴት መምጣት እንደሚችል በተግባር ያሳየችውን አዲስ አበባን ለመጎብኘትና ልምድ ለመቅሰም የመጣነው በማለት ገልፀዋል፡፡

በከተማዋ የተከናወኑ የልማት ኘሮጀክቶች በሀገር ውስጥ መሃንዲሶችና የሥራ ተቋራጮች የተሰሩ መሆናቸው አንዱ የጐብኝዎችን ትኩረት የሳበው ጉዳይ መሆኑን የገለጹት የኢትዮጵያ ሪል እስቴት አልሚዎች ማህበር ምክትል ኘሬዝዳንት አቶ ጀበል ጀማል ናቸው፡፡

ጐብኝዎቹ የኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻ ኘሮጀክቶችና ሌሎች የልማት ሥራዎች ላይ ልምድ አግኝተው በሀገራቸው ከተሞች ላይ ለመተግበር መፈለጋቸውን ተገንዝበናል ብለዋል፡፡

የቢጃይ ቢዝነስ ግሩኘ መስራችና ባለቤት ኢ/ር ቢጃይ ናይከር በበኩላቸው በከተማዋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ 24 ሰዓት የመስራት ልምድ እና ኘሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት ሰርቶ ማስረከብ ልምድ እየሆነ በመምጣቱ ብዙ ነገር አትርፈናል ብለዋል፡፡

በዚህም ንጹህ አካባቢን፣ ሳቢ እና የሚያምር ከተማን ሰርተናል ይህም የጐብኝዎችን ቁጥር በማሳደግ የቱሪዝም ፍሰቱን የሚጨምር ነው ብለዋል፡፡

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review