የልብ በሽታ በዓለም ላይ በየዓመቱ ከ19 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ህይወት በድንገት ይቀጥፋል፡፡
በገዳይነቱም ቢሆን በቀዳሚነት እንደሚቀመጥ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ያመለክታል፡፡
የልብ ድካም ህመም ምልክቶቹ በአብዛኛው ከሌሎች በሽታዎች ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው በመሆኑ የበሽታው ተጠቂዎች እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ የችግሩ ተጠቂ መሆናቸውን አያውቁም፡፡
ይህ ደግሞ የልብ ድካሙ ከተከሰተ በኃላ የመዳን እድሉን ያጠበዋል፡፡

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፒሻሊስት ሀኪም የሆኑት ዶ/ር ሙባረክ ዘይኑ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ህመሙ በልብ ውስጥ ደም አስተላላፊ የደም ስሮች ሲጠቡ ወይም ሙሉ በሙሉ ሲዘጉ የሚከሰት የጤና ችግር መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር ሙባረክ ዘይኑ በቆይታቸው፣ የልብ ትርታ ከተለመደው ውጪ መሆን፣ በተደጋጋሚ የሚከሰት የራስ ማዞር፣ የሚዛን መሳት፣ የእይታ ብዥታ፣ የልብ ጡንቻ መላላትና አቅም ማጣት፣መሀል ደረትን የመጨምደድና የመጭነቅ ስሜት የልብ ድካም ህመም ምልክቶች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም ድንገት የሚከሰት ቀዝቃዛ ላብ፣ ምንም አይነት አድካሚ አንቅስቃሴ ሳይደረግ በተደጋጋሚ የሚከሰት ድካምና አቅም ማጣት፣ የትንፋሽ ማጠር፣ በእግር በተለይ በቁርጭምጭሚት ላይ ማበጥና የልብ ምት መዘበራረቅ ከምልክቶቹ ውስጥ የሚካተቱ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ ጊዜ አንጐል ትክክለኛ ተግባሩን ለመወጣት የሚቸገር በመሆኑ፣ ህመሙ ከቁጥጥር ውጪ ይሆናል ነው ያሉት፡፡
የልብ ድካም ህመም ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ በብዛት የሚከሰት ሲሆን፤ በተለይ በሴቶች ላይ የልብ ድካም ሊከሰት መሆኑን የሚያመላክቱ በአገጭ እና በአንገት አካባቢ የህመም ስሜት፣ የማያቋርጥ ሳል፣ ማስመለስ እና በሆድ አካባቢ ከፍተኛ ህመም ይኖራል፡፡
በልብ ድካም የሚከሰት ድንገተኛ ሞትን እና የከፋ ጉዳትን ለመከላከል፣ ጭንቀትንና የኮሊስትሮል መጠንን መቀነስ፣ የደም ግፊት እና የስኳር መጠንን መቆጣጠር፣ ሲጋራ አለማጨስ እና በቂ እንቅልፍ ማግኘት እንደሚገባም ዶ/ር ሙባረክ ዘይኑ መክረዋል፡፡
በበሽታው የተጠቁ ሰዎች ጊዜ ሳይሰጡ በአፋጣኝ ወደ ጤና ማዕከል በመሄድ የጠበበው ወይም የተዘጋውን የልብ ቧንቧ በቀዶ ጥገና እንዲስተካከል እና 325 ሚሊ ግራም አስኘሬን ኪኒን እንዲጀምሩ በማድረግ እንዲሁም የሚሰጠውን መድሃኒት ያለማቋረጥ መውሰድ እንዲችሉ በማድረግ በሽታውን ማከም እንደሚቻል ዶ/ር ሙባረክ ዘይኑ አስገንዝበዋል፡፡
በበረከት ጌታቸው