ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የባህር በር ባለቤት ብትሆንም አግባብነትና ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የባህር በር ማጣቷ በርካታ ኢትዮጵያዊያንን ለቁጭት ከዳረገ አመታት ተቆጥረዋል፡፡
ኤኤምኤን ያነጋገራቸዉ አንዳንድ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም ኢትዮጵያ ለአመታት ህጋዊና አግባብነት በሌለዉ መንገድ የባህር አጥታ መቆየቷ እንዳሳዘናቸዉ ይገልጻሉ፡፡

በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚደራደር ሰው የለም ያሉት የመዲናዋ ነዋሪ አቶ ሱልጣን አብዱልቀድር አብርሃ የለዉጡ መንግስት ያነሳዉ የባህር በር ጥያቄ ተገቢና ወቅታዊ መሆኑን ያነሳሉ፡፡
ወደ ሃገር የሚገቡትም ሆነ ከሃገር የሚወጡ ሸቀጦች የሚተላለፉት በወደብ በኩል ነው ያሉት አቶ ሱልጣን፤ ኢትዮጵያ የራሷ ወደብ በማጣቷ በርካታ ፈተናዎችን እየተጋፈጠች ነዉ ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአሁን ቀድም ለጎረቤት ሀገራት ጭምር የሚጠቅም ጠንካራ የባህር ኃይል እንደነበራት በመግለጽ የባህር ኃይሉ አግባብነት በሌለዉ መንገድ መበተኑ ቁጭት እንደፈጠረባቸዉም ገልጸዋል፡፡
መምህርት ቅድስት ብርሃኑ በበኩላቸዉ የባህር በር ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት፤ ሉአላዊነትና ደህንነት ወሳኝ ሚና እንዳለዉ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የባህር በር ተጠቃሚ እንደነበረች እና ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ይህን ዕድል ማጣቷን ያነሱት መምህርት ቅድስት፣ አሁን መንግስት ያነሳው አጀንዳ ተገቢና ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ከመንግስት ጎን በመሆን ሊደግፍ ይገባል፤ ኢትዮጵያም የባህር በር ማግኘት ይኖርባታል ብለዋል፡፡

የቀድሞ የባህር ኃይል አባል አቶ ተስፋሁን አሰፋ፣ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በጣም ወሳኝ እና ወቅታዊ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ አግባብነት በሌለዉ መንገድ የአሰብ ወደብን ብትነጠቀም አሁን ላይ ግን ህጋዊ በመሆነ መንገድ የባህር በር የማግኘት መብቷ ሊከበር ይገባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያነሳችዉ የባህር በር ጥያቄ ከታሪክም ሆነ ከህግ አንጻር ተቀባይነትና አግባብነት ያለዉ በመሆኑ የባህር በር ለኢትዮጵያ ይገባታል፤ ለተፈጻሚነቱም ሁሉም ዜጋ ከመንግስት ጎን ሊቆም ይገባል ብለዋል፡፡
በታምራት ቢሻው