ብዝኃነት ለኢትዮጵያ እድገትና ልማት መሰረት መሆኑ ተገለጸ።
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት ህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም በሆሳዕና ከተማ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ።
በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽ/ቤት የሕገ-መንግስት እና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኃይለየሱስ ታዬ (ዶ/ር) በዓሉን አስመልክቶ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ብዝኃነት ለኢትዮጵያ እድገትና ልማት መሰረት መሆኑን ገልጸዋል።

ዘንድሮ በሆሳዕና ከተማ የሚከበረው የብሔሮች ብሔረሰቦች ቀን ኢትዮጵያ የሃይሏ ምንጭ የሆነውን ብዝኃ ማንነቷን ለዓለም የምታሳይበት ፣ የዜጎቿን ወንድማማችነት የምታጠናክርበት ብሎም ለሃገረመንግስት ግንባታ መሰረት የሆነው አንድነት ጎልቶ የሚታይበት በዓል መሆኑንም ጠቁመዋል ።
ብዝኃነትን መረዳት እና እውቅና መስጠት ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ብሎም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉትም ዋና ዳይሬክተሩ አንስተዋል።
በዓሉ ዜጎች ስለፌደራሊዝም እና ደሞክራሲ ያላቸውን ግንዛቤ ከማስፋት ባለፈ አንዳቸው የሌላኛውን ባሕል ለመረዳት ዕድል የሚሰጥና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትሥሥራቸውን እንዲያጎለብቱ የሚያግዝ መሆኑን ነው ኃይለየሱስ ታዬ የገለፁት (ዶ/ር) ።
በወርቅነህ አቢዮ