ወደብ ኖሮን ነገር ግን በታሪካዊ ስህተት የተነጠቅን ነን ሲሉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ተውፊቅ አብዱላሂ (ዶ/ር) ተናገሩ ፡፡

ወደብ ለአንድ ሃገር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳለዉ የተናገሩት አምባሳደር ተውፊቅ የወደብ ጉዳይ ለኢትዮጵያ ቅንጦት ሳይሆን የህልውናና የደህንነት ጉዳይ ነው ሲሉ ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልፀዋል፡፡
እኛ ከሌላው ዓለም ጋር የምንገናኝበት እና መተላለፊያችን ቀይ ባህር ነው ስለሆነም ቀይ ባህር ለህልውናችን መሰረት ነው ብለዋል ፡፡

ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ተያይዞ የባህር በር አለመኖር ለተደራራቢ ታሪፍ እና የአገልግሎት ክፍያ ከመዳረጋችን በተጨማሪ በሌሎች ሃገራት ላይ ጥገኛ በማድረግ በምርት ግብይት ላይ ተግዳሮት እንዲከሰት ምክንያት ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል ፡፡

በባለ ወደብ ሃገራት የሚፈጠሩ የሰላም እና የፖለቲካ ችግሮች በወጪና ገቢ ሸቀጦችና በአጠቃላይ የሸቀጦች እንቅስቃሴዉ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንደሚያስከትሉ ጠቁመዋል።
የዉጭ ኢንቨስተሮችን ወደ ሃገር ቤት ለመሳብ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማሳደግ ወደብ የማይተካ ሚና እንዳለው ያነሱት አምባሳደሩ ወደብ ለኢትዮጵያ ቅንጦት ሳይሆን የህልውናና የዕድገት ጉዳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል ፡፡
በያለው ጌታነህ