መጠገን የሚሻው ስብራት

You are currently viewing መጠገን የሚሻው ስብራት

ኢትዮጵያ ያለአግባብ ያጣችውን የባሕር በሯን የመጠየቅ ሕጋዊ፣ ፍትሐዊ እና ታሪካዊ መሠረት እንዳላት ተመላክቷል

ኢትዮጵያ ዐባይን እንደ መቀነት ታጥቃ፣ ቀይ ባህርን እንደ ጋቢ ተከናንባ፣ ብዙ ህዝብ፣ አያሌ ታሪክ እና እውነትን አንግባ እንዴት የባሕር በር አጣች? የሚለውን ስናስብ፣ የሆነብንና የሆነልን ሁሉ ሲተነተን ውስብስብነት አያጣውም።

በ1983 ዓ.ም ስልጣን የተቆጣጠረው ኃይል የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል እንዲፈርስ አደረገ። በዚያች ክፉ ቀን እንዲህ ሆነ፡፡ ጥቂቶች ግን ቆፍጣናዎቹ  የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አባላት የባሕር በራችንን አናስደፍርም ብለው ደንጎሎ ላይ አሸለቡ፤ በእምባትካላ ወደቁ፡፡ በምፅዋ እና በአሰብ ረገፉ፤ የተረፉትም በሳህል በርሃ ሞቱ። ብዙዎቹም ከሀገር በላይ ምንም! ብለው በየተራ ተሰው።

የሀገር ልጆች፣ እነዚያ የማር እጆች፣ በማወቅም ባለማወቅም በተተበተበ የሴራ ሰንሰለት ተጠለፉ፡፡ እነዚያ እንቁዎች፣ የሀገር ማገሮች፣ ጀግናና ገራገሮቹ፣ ባለ ሀገሮቹ ቀይ ባሕርን፣ አሰብ ወደባቸውን የባሕር ድንበራቸውን በስስት እና በመራር ጀግንነት እየተመለከቱ የሀገር ፍቅርን በንግግር ሳይሆን በተግባር እየተረኩ ነጎዱ፤ ያን ክፉ ቋጠሮ ዘመን እስኪገልጠው ትውልድ እስኪፈታው፡፡

አዎን፣ ኢትዮጵያ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን በ1948 ዓመተ ምህረት የተቋቋመና እስከ ደርግ ዘመን ማብቂያ የቆየ የባሕር ኃይል ነበራት፡፡ በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን የአሜሪካና የሩሲያን መርከቦች ጎን ለጎን ያሰለፈ፣ ጥቂት ግን ውጤታማ ሲል ዓለም የመሰከረለት፣ ከራስ ካሳር እስከ ራስ ዱሜራ ያለውን የውሃ ክልል በልሕቀት ያስከበረ ቆፍጣና የባሕር ኃይል ነበራት፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል መርከበኛ፣ የሕክምና ባለሙያ፣ ገጣሚና ተርጓሚ ሊዲንግ ሲማን አለማሁ ማሞ ‘ጥቂቶቹ’ በተሰኘ መፅሐፋቸው እንዲህ አሉ፡፡ “መዋኛ ገንዳ ውስጥ ስገባ ይሁን ጀልባና መርከብ ላይ በወጣሁ ቁጥር ባሕረኞች ባልደረቦቼን አጠገቤ እንዳሉ አድርጌ እዘክራቸዋለሁ፡፡”

የቀድሞው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ሰራዊት የቃል ኪዳን ሕብረ ዝማሬ በተለያዩ መድረኮች አሊያም በማህበራቸው መታሰቢያ መርሃ ግብሮች ‘መልህቅ ዓርማዬ ቀይ ባሕር ቤቴ  ጀግንነት ውርሴ ያባት ያያቴ’ የሚለው ዝማሬ ሲሰማ ከልብ የፈለቀ የሚያቃጥል ዕምባ እንደ ዥረት ሲወርድ ይታያል፡፡

በእርግጥ በማይገባ መልኩ ከቀይ ባሕር የራቅንበት በተለይም የአሰብ ወደብን ያጣንበት መንገድ በግለሰብ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ሊዘከር ይገባው ነበር። ግን ከለውጡ በፊት በነበረው መንግስት ይህ ፈፅሞ ሊታሰብ ይቅርና አጀንዳውን በተለያዩ መድረኮች ያነሱ ምሁራን ይታሰሩ አሊያም ይሰደዱ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡

የዓለም ሕግና ታሪክ ግን የሚነግረን ከዚህ ባሻገር ያለውን ደማቅ እውነት ነው። ለአብነትም የደቡብ አሜሪካዋ ሀገር ቦሊቪያ፣ እ.ኤ.አ ከ1879 እስከ 1884 በቆየው  ፓስፊክ ጦርነት፣ የፓስፊክ የባሕር ዳርቻዋን እና የወደብ ከተማዋን አንቶፋጋስታ በቺሊ ካጣች በኋላ ወደብ አልባ ሀገር ሆነች።

ይህም ታሪካዊ ኪሳራ ብሔራዊ ቁጭት፣ ሰቀቀን እና ትዝታ፣ ትዝታም ብቻ ሳይሆን መልሶ የማግኘት ወኔን በሚቀሰቅስ መልኩ ቦሊቪያውያን ሁሌም መጋቢት 23 ቀን  “ዲያ ዴል ማር” ወይም “ብሔራዊ የባሕር ቀን”  እያሉ  ለ146ኛ ጊዜ ባሕር ያጡበትን ቀን እያከበሩት ነው፡፡ አዎ  ቦሊቪያ በደቡብ አሜሪካ የባሕር በር ከሌላቸው ሁለት ሀገራት አንዷ ናት፡፡ ነገር ግን በየዓመቱ መጋቢት 23 ቀን የምታከብረው ይህ በዓል  ቺሊ በጦርነት የነጠቀቻትን 250 ማይል የፓስፊክ የባሕር ዳርቻን እያስታወሰች “ታሪካዊ ኢ ፍትሐዊነትን” ትዘክርበታለች፤ ትሞግትበታለች። ዜጎቿንም ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን ኢ ፍትሐዊነት የነጠቃቸውን የባሕር በር ለማስመለስ የሚደረገውን ሁለንተናዊ ጥረት እንዲያግዙ ታበረታታበታለች፡፡

ታይም መፅሔት እ.ኤ.አ ጥቅምት 3 ቀን 2018 “ላንድሎክድ ቦሊቪያ ወንትስ ኤ ፓዝ ቱ ዘ ፓሲፊክ” (Landlocked Bolivia Wants a Path to the Pacific) በሚል ርዕስ ባሰፈረችው ሰፋ ያለ ትንታኔ በዚሁ ዓመት ጥቅምት 1 ቀን የተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የፍትህ ፍርድ ቤት (ICJ) ቺሊ ለጎረቤቷ ቦሊቪያ ወደ ባሕር የሚያደርስ መንገድ እንድትሰጥ ለማስገደድ ውሳኔ አስተላልፏል። በዋና ከተማዋ ላ ፓዝ በሚገኙ ትላልቅ የከተማ አደባባዮች ዙሪያ የተሰበሰቡ የቦሊቪያ ነዋሪዎችም እ.ኤ.አ ከ1879 ጀምሮ ባልተገባ መልኩ ያጡት የባሕር በራቸው ብሶት ውስጣቸውን እየለበለበው ቢሆንም ውሳኔውን ልብን በሚፈነቅል የደስታ ስሜት ተመልክተውታል ይላል የታይም ዘገባ፡፡

እናም ፍርደ ገምድል የሆነው ዓለም ፊቱን እስኪያዞር፣ አሊያም ዘመን የወሰደውን ዘመን እስኪመልሰው እና ትውልድ እስኪያድሰው ቦሊቪያ እ.ኤ.አ በ1963 ከአሜሪካ እና ከቻይና የተጣሉ መርከቦችን በመጠቀም “አርማዳ ቦሊቪያና” በሚል ስያሜ የባሕር ኃይሏን መስርታለች፡፡ ከ5 ሺህ በላይ ወታደሮቿም በአማዞን እና በቲቲካካ ሐይቅ ላይ በሚደረጉ ልምምዶች ይሳተፋሉ። እንዲሁም የቦሊቪያን የወንዝ ድንበሮች ከብራዚል፣ ከፓራጓይ እና ከአርጀንቲና ጋር ይጠብቃሉ። እንደ ታይም መፅሔት ዘገባ ቦሊቪያ በዓለም አቀፍ ባሕር ሕግም፣ በጂኦፖለቲካል እሳቤም በታሪክ እና በምጣኔ ሀብታዊ ምልከታም ወደብ የማግኘት መብት አላት፡፡

ኢትዮጵያ ደግሞ ያጣችው በዓለማችን የንግድ፣ የፖለቲካ እና መሰል ጉዳዮች መለኪያ ‘የዓለማችን እስትንፋስ አሊያም ጉሮሮ’ የሚባለውን ቀይ ባሕርን ነው። ለአብነትም የቀይ ባሕርና አካባቢ የዓለማችን ከ30 በመቶ በላይ የንግድ ልውውጥ የሚደረግበት፣ ኃያላኑ ባለው ጂኦፖለቲካል ፋይዳ የጦር ካምፖቻቸውን የመሰረቱበትና ጦራቸውንም የሚያርመሰምሱበት፣ የሚሻኮቱበት፣ ጡንቻ የሚለካኩበት ነው፡፡

እናም የሀገሬ ሰው “በፍርድ ከሄደች በቅሎዬ፣ ያለፍርድ የሄደች ጭብጦዬ” እንዲል፣ ያለ ፍርድ አሊያም ያለ አግባብ ያጣነውን የባሕር በራችንን መጠየቅ ሕጋዊም፣ ፍትሐዊም መሆኑን የቦሊቪያ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ የባሕር በር አልባ ሆና የቆየችው ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር በኩል የባሕር መተላለፊያ ማግኘት አለባት የሚል ቆራጥና ትክክለኛ አቋም የያዘው የለውጡ መንግስት በተደጋጋሚ ፍላጎቱን ሲገልጽ ቆይቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ “ኢትዮጵያ የማይናወጥ ብሔራዊ ጥቅም አላት፤ ዓለም ዛሬ ይስማ…የቀይ ባሕር በር ኢትዮጵያ ያስፈልጋታል፤ በማንኛውም ህግ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ይገባታል፤ ብዙዎች እኮ ነውር ነው ይላሉ፤ 120 ሚሊዮን ህዝብ ላይ ባሕር እንዳያይ መቆለፍ ትክክል አይደለም፡፡” በማለት ጉዳዩን በአፅንኦት መግለፃቸው የዚሁ ማሳያ ነው፡፡

በቀይ ባሕር ክልል ወሰነ-ሰፊ ይዞታ የነበራት ኢትዮጵያ፣ በየዘመናቱ ህዝቦቿ በከፈሉት መሪር መስዋዕትነት ነፃነቷንና ክብሯን ጠብቃ የኖረች ሀገርም ነች። አዱሊስ፣ ዘይላ እና ምፅዋ ወደቦችም በኢትዮጵያ ግዛት ሥር እንደነበሩ በርካታ የታሪክ ሰነዶች ያረጋግጣሉ። ለአብነትም ያዕቆብ ኃ/ማርያም (ዶ/ር) በመስከረም ወር 2004 ዓ.ም “አሰብ የማን ናት?” በሚል ርዕስ ለህትመት ያበቁትን መጽሐፍ መጥቀስ እንችላለን፡፡

ደራሲው በመጽሐፋቸው እንደ ሀገር ከቀይ ባሕር የተገለልንበት መንገድ ኢ ፍትሐዊ መሆኑን በዓለም አቀፍ ሕግጋትም ተመልሰን የማግኘት ግልፅ መብትና እውነት እንዳለን ገልፀዋል፡፡ በሌላ በኩልም “የኢትዮጵያን የባሕር በር (አሰብን) ማስመለስ የሁሉም የሀገሪቱ ዜጋ ብሔራዊ ግዴታ ነው፤ ይህም እንዲሆን እያንዳንዱ ዜጋ አቅሙ የሚፈቅደውንና የሚችለውን እንዲያደርግ”  ሲሉም ይማፀናሉ፡፡

ኢትዮጵያ በታሪኳ ያለፈቻቸው መነሳትና መውደቅ ከባሕር ጋር ከነበራት ቅርበትና ርቀት ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት አለው። የባሕር በሮቿ በእጇ በነበሩበት ዘመን የጎለበተችና የበለፀገች ኢትዮጵያን መመስረት ተችሏል። በአንፃሩ የባሕር በሯን በተነጠቀችባቸው ዘመኖች ኢኮኖሚዋ የኮሰሰ፣ ፖለቲካዋ የተናጋ ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ አይተናል።

ያዕቆብ ኃ/ማርያም (ዶ/ር) በቀጣናው በህዝብ ብዛት ቁጥር ግዝፈቷና ለባሕር ባላት ቅርበት የመጀመሪያ የሆነችው ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሀገር መሆን እንደማይገባት ነው በመጽሐፋቸው በብርቱ የሚሟግቱት። የሙግታቸው ዋነኛ ትኩረትና ማነጣጠሪያቸው አሰብ ወደብ ነው። በአልጀርሱ ሥምምነት፣ የአሰብ ወደብ ባለቤትነት መብቷን የምታስከብርበትን መልካም አጋጣሚ መጠቀም አለመቻላችን የሚያስቆጭና በወቅቱ የነበረውን ሴራ የሚያመላክት ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ይህን ጉዳይ አንስተው አብራርተዋል። በማብራሪያቸውም፣ የኢትዮጵያን የቀይ ባሕር ድንበርተኝነት ያሳጣው ውሳኔ በማን እንደተወሰነ የሚያሳይ የሰነድ ማስረጃ አለመገኘቱን ጠቅሰው፣ ውሳኔው ሕጋዊ እንዳልሆነ አመላክተዋል፡፡

ታድያ እንዲህ ያለው ጉዳይ ከህግ አግባብ እንዴት ይታያል ያልናቸው የህግ ባለሙያው አቶ ኪያ ፀጋዬ፣ በወቅቱ የነበረው የሽግግር መንግስት እንደመሆኑ የባሕር በርን በሚያህል ጂኦ እስትራቴጂካዊ ጉዳይ ላይ ውሳኔ የመስጠት ስልጣን የለውም፡፡ ስለዚህ ውሳኔው ህጋዊ መሠረት የለውም በማለት ጉዳዩን አብራርተዋል፡፡

የህግ ባለሙያው በማብራሪያቸው፣ እንዲህ ያለውን ውሳኔ ለማሳለፍ የሚችል ህጋዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ባልተመሰረተበት ሁኔታ ነው ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ያጣችው፤ ተቀባዩም ሆነ ሰጪው ከጫካ የመጡ የጋራ ዓላማ የነበራቸው ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊ ውግንና ቢኖራቸው ኖሮ በሺህ ኪሎ ሜትሮች የሚቆጠር ርዝመት ያለው የባሕር በር ያላትን ሀገር በአንድ ጀንበር ዝግ አያደርጓትም ነበር። ስለዚህ ህዝብ ተወያይቶ ያልደረሰበት ስምምነት እና በህዝብ የተመረጠ መንግስት በሌለበት የተላለፈ ውሳኔ በመሆኑ ህጋዊ መሠረት እንደሚያሳጣውም ጠቅሰዋል፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review