የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ከሚሽን ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ
ሀገራዊ ጉባኤ ማከናወንና በምክክሩ የሚገኙ ምክረ ሀሳቦችን ለሚመለከታቸው አካላት ማቅረብ ከቁልፍ ስራዎች መካከል እንደሆኑ ተመላክቷል
ኢትዮጵያ በዓለም ጥቁር ህዝቦች ዘንድ ደማቅ ታሪክ ያላት ሀገር ናት፡፡ በተለይም ህዝቦቿ የሀገር ሉዓላዊነትንና ነፃነትን በተጋድሎ አስጠብቀው በማስቀጠል ይታወቃሉ፡፡ ለዚህ ቀደምቶቻችን ካስመዘገቧቸውና ታሪክ እየዘከራቸው ከሚገኙት መካከል የዓድዋ እና የካራማራ ድሎችን እንደ አብነት መጥቀስ ይቻላል። የአሁኑ ትውልድም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በማጠናቀቅ በዓባይ ወንዝ ላይ ልማት የማካሄድ የዘመናት ህልምን ወደ ተግባር መቀየር ችሏል፡፡
ኢትዮጵያ እነዚህንና ሌሎች ወርቃማና አኩሪ የታሪክ ውርሶች፣ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥርና ትልቅ አቅም ያላት ሀገር ብትሆንም መድረስ ከሚገባት ቦታ መድረስ አልቻለችም፡፡ ግጭትና ድህነትም ሌላኛው መገለጫዋ ሆነው ቀጥለዋል፡፡ ለዚህም በየጊዜው እየተንከባለሉ የመጡ፣ በተለያዩ የፖለቲካ ሊሂቃን፣ በመንግስትና ህዝብ እንዲሁም በማህበረሰብ መካከል በተለያዩ ሀገራዊ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ የሚታዩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች እንደምክንያት ይነሳሉ፡፡ እነዚህ ለግጭት ምክንያት በመሆን በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት ከማድረስም ባለፈ የሀገርን ህልውና አደጋ ውስጥ እየከተቱ መምጣታቸውን ምሁራንና መንግስት በተደጋጋሚ ሲናገሩ መስማት አዲስ አይደለም፡፡
የማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪው ብርሃኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) “ብሔርተኝነት” በተሰፕው መጽሐፈቸው ላይ እንዳሰፈሩት፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካና ማህበራዊ ቀውሶች ዋነኛ ምክንያት ዜጎች የተሰማሙብት የጋራ ሀገራዊ ማንነትና መገለጫዎች አለመኖር ነው። የወል ወይም የጋራ ማንነት መገንባት እንደሀገር አብሮ ወደፊት ለመሄድ እጁግ ወሳኝ እርምጃ ነው። ለዚህም ሀገራዊ ምክክር ዋነኛው መፍትሔ ነው።
ርሃኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) “ብሔር-ተኝነት” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንዳሰፈሩት፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካና ማህበራዊ ቀውሶች ዋነኛ ምክንያት ዜጎች የተስማሙበት የጋራ ሀገራዊ ማንነትና መገለጫዎች አለመኖር ነው፡፡ የወል ወይም የጋራ ማንነት መገንባት እንደሀገር አብሮ ወደፊት ለመሄድ እጅግ ወሳኝ እርምጃ ነው፡፡ ለዚህም ሀገራዊ ምክክር ዋነኛው መፍትሔ ነው፡፡
ከሶስት ዓመት በፊትም በመንግስት ተነሳሽነት በኢትዮጵያ መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችና አለመግባባቶች መነሻ ምክንያቶችን በመለየት፣ በተለዩ አጀንዳዎች ላይ ምክክር እንዲካሄድ እንዲሁም የተገኙ ምክረ ሀሳቦችን እንዲተገበሩ በማድረግ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር ሂደቱን የሚያስተባብር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንዲቋቋም ተደርጓል። ኮሚሽኑ ከተቋቋመ በኋላ ስራውን በሶስት ዓመታት ውስጥ እንዲያጠናቀቅ ቀነ ገደብ ተቀምጦለት የነበረ ቢሆንም ከስራው አዲስነት፣ ሂደቱን አካታችና አሳታፊ ማድረግ ስለሚገባና በአንዳንድ አካባቢዎች ከነበረው የሰላምና ደህንነት ችግር አኳያ በተያዘው ጊዜ ማጠናቀቅ አልተቻልም፡፡ በዚህም የተነሳ ቀሪ ስራዎችን እንዲያጠናቅቅ የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የስራ ዘመን የካቲት 2017 ዓ.ም ላይ ለተጨማሪ አንድ ዓመት ማራዘሙ ይታወሳል፡፡

የኮሚሽኑ ቀሪ ስራዎች
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት ሀገራዊ ምክክሩን ለማካሄድ የቅድመ-ዝግጅት፣ ዝግጅትና ሂደት ምዕራፍ ስራዎች ረዘም ያለ ጊዜ ወስደዋል፡፡ ምክንያቱም የስራዎቹ በትክክል መከናወንና አለመከናወን በምክክሩ ሂደትና ውጤታማነቱ ላይ የራሱ የሆነ አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖ አላቸው፡፡ በአሁኑ ወቅትም በምክክሩ የሚሳተፉ ባለድርሻ እና ተባባሪ አካላትን በመለየትና ተሳታፊዎችን በመምረጥ የአጀንዳ ሀሳቦችን የማሰባሰብ ስራ ከትግራይ በስተቀር በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ማጠናቀቅ ተችሏል፡፡
በ2018 ዓ.ም የሀገራዊ ምክክሩ ቀሪ ስራዎች ለማጠናቀቅ በዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ምክክሩ አሳታፊና አካታች እንዲሆን ከሀገር ውስጥ ባለፈ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በማሳተፍ አጀንዳ የማሰባሰብ፣ የትግራይ ክልልን በምክክሩ ሂደት የማሳተፍ፣ በተለያየ ምክንያት ያልተሳተፉ ሀይሎች (የፖለቲካ ፓርቲዎችና የታጠቁ ሀይሎች) በምክክሩ ሂደት ማሳተፍ፣ አጀንዳ መቅረፅ፣ ሀገራዊ ጉባኤ ማከናወንና በምክክሩ የሚገኙ ምክረ ሀሳቦችን ለሚመለከታቸው አካላት ማቅረብ የሚሉ ዋና ዋና ቁልፍ ስራዎች ይከናወናሉ፡፡
በቅርቡም ኮሚሽኑ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን (ዳያስፖራዎች) የአጀንዳ ሀሳብ ማሰባሰብና ተወካዮችን የመምረጥ ተግባር አከናውኗል፡፡ ኮሚሽነር ሙሉጌታም ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን በደቡብ አፍሪካ፣ በሰሜን አሜሪካ እና በካናዳ በተካሄዱ የምክክር መድረኮች ላይ በማስተባበርና በመምራት ተሳትፈዋል፡፡ እሳቸው እንደገለፁት፣ በእነዚህ አገራት በተካሄዱ መድረኮች ከዳያስፖራው ማህበረሰብ አጀንዳ የማሰባሰብ ስራው በስኬት ተከናውኗል። ተሳታፊዎቹ በኢትዮጵያ ለሰላም እጦት ምክንያት ናቸው ያሏቸውን ችግሮች በአጀንዳ ሀሳብነት እንዲያዙ አንስተዋል፡፡ በተጨማሪም በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ በእንግሊዝ ለንደን እና በስዊድን ስቶክሆልም ከሚኖሩ ዳያስፖራዎች ጋር በመገናኘት የአጀንዳ ሀሳብ የማሰባሰብና በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ላይ የሚሳተፉ ተወካዮች መረጣ ተከናውኗል፡፡
ሌላውና የዓመቱ ቁልፍ ስራ በትግራይ ክልል የአጀንዳ ሀሳብ ማሰባሰብ ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ሰብሳቢ መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) በአዲሱ ዓመት መግቢያ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ማብራሪያ፣ ኮሚሽኑ በክልሉ የአጀንዳ ሀሳብ ማሰባሰብ ስራዎችን ለመጀመር የተለያዩ ጥረቶች ሲያካሄዱ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ የምክክር ሂደቱን ለመጀመር ኮሚሽኑ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ኃላፊዎች፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኒ፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራትና ምሁራን ጋር ውይይቶችን አድርጓል፡፡ በቅርቡም ኮሚሽኑ በክልሉ ከሚገኙ የሚዲያ ባለሙያዎች ጋር የውይይት መድረክ አድርጓል፡፡
“ይህን እያደረግን ያለነው ‘ነገ ወይም ወዲያውኑ ሀገራዊ ምክክሩን ወደእናንተ እናምጣው፤ አጀንዳ እንሰብሰብ’ በሚል ሁኔታ ውስጥ አይደለም፡፡ በአሁኑ ሰዓት በትግራይ እያደረግን ያለነው መተማመንን የመፍጠር (Confidence Building) ተግባር ነው፡፡ በክልሉ በነበረው ጦርነት ክልሉ እና የፌዴራል መንግስት አይገናኙም ነበር፡፡” ያሉት መስፍን (ፕሮፌሰር) ባለድርሻ አካላት የኮሚሽኑን ዓላማውንና ተአማኒነቱን እንዲረዱ፣ ሀገራዊ ምክክር የትግራይንም ሆነ የሌሎች ኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄዎች መፍታት የሚያስችል ሂደት መሆኑን እንዲገነዘቡ የማድረግ ስራ መሰራቱን አንስተዋል፡፡ በትግራይ ክልል የምክክሩን ሂደት ለመጀመር መተማመን በመፍጠር ረገድ የተሻለ ስራ ተሰርቷል፡፡ ወደ ምክክር ሂደቱ ከተገባ በክልሉ ያሉ 94 ወረዳዎችን በሁለት ሳምንት ውስጥ መድረስ እንደሚቻል አክለዋል፡፡
ሌላው ኮሚሽኑ በቀሪ ጊዜያት የሚያከናውነው ተግባር በተለያየ ምክንያት በምክክር ሂደቱ እየተሳተፉ የማይገኙ አካላት ወደ ምክክሩ እንዲገቡና የአጀንዳ ሀሳባቸውን እንዲያቀርቡ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ረገድ አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምክክሩ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ ኮሚሽነር ሙሉጌታ እንደሚሉት፣ ጥቂት የፖለቲካ ፓርቲዎች በኮሚሽኑ ተአማኒነት፣ የሀገራዊ ምክክሩ ሂደትና ውጤታማነት ላይ ጥያቄ በማንሳት በሂደቱ እየተሳተፉ አይደለም። እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምክክሩ ሂደት እንዲሳተፉ ኮሚሽኑ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚገኙበት መድረክ እና በተናጠል ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
በኮሚሽኑ ገለልተኝነት ላይ ጥርጣሬ ያላቸው ወገኖችም ቀረብ ብለው ጥያቄ እንዲያቀርቡ፤ የተሳታፊዎች ልየታና የአጀንዳ አሰባሰብ ላይም ክፍተት አለ ካሉ በሂደቱ በመሳተፍ መገምገም እንደሚችሉ ኮሚሽኑ አሳውቋል፡፡ ከዚህ ውጪ ኮሚሽኑ “ተፅዕኖ ይደረግበታል” የሚል ግምት በመያዝ ወደኋላ መቅረት ተገቢነት የለውም፡፡ “ገዥውም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ ስልጣን መምጣት የሚችሉት ሀገር ሲኖር ብቻ ነው፡፡ የሰላም እጦት፤ እርስ በእርስ መተማመን በጠፋበት፤ በየትኛውም ሁኔታ ስልጣን ላይ የሚወጣ አካል ሀገርን መምራት አይችልም፡፡” ሲሉ ኮሚሽነር ሙሉጌታ አንስተዋል፡፡
በምክክሩ ሂደቱ የታጠቁ ሀይሎች እንዲሳተፉ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲተላለፍ መቆየቱን ኮሚሽነር ሙሉጌታ ያነሳሉ። ኮሚሽኑ እነዚህ ሀይሎች ወደ ግጭትና ጦርነት ያስገባቸው ምክንያት ምን እንደሆነ እንዲያነሱና ምክክር ተደርጎባቸው እና ለሚመለከታቸው አካላት ቀርበው ይፈቱ ዘንድ የአጀንዳ ሀሳባቸውን እንዲያቀርቡ ከመንግስትና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት (የሰላም ኮሚቴዎች) ጋር በመነጋገር ሲሰራ ቆይቷል፡፡ የሚቀርቡ የተሳተፉ ጥሪዎች የማይፈፀሙ ሳይሆኑ የሚተገበሩ፤ በታሪክ ማህደር ውስጥ የሚመዘገቡ፣ ነገ የኢትዮጵያ ህዝብ አይቶ ፍርድ የሚሰጥበት በመሆኑ እነዚህ ሀይሎች አጀንዳቸውን ቢያቀርቡ ለሀገራዊ ችግሮች መፍትሔ የሚመጣበት ሁኔታ እንደሚኖር ኮሚሽነር ሙሉጌታ አስገንዝበዋል፡፡

“ኮሚሽኑ የአጀንዳ ሀሳብ እንዲቀርብ ለሁሉም በሩን ክፍት አድርጎ እየሰራ ነው፡፡ ስልጣን ላይ ያለ አካል ወይም በምርጫ ወደ ስልጣን ለመምጣት የሚፈልግ አካል በሀገር ጉዳይ ላይ ለመነጋገር በማኩረፍ ወደኋላ መቅረት የለበትም፡፡ አንዳንድ አካላት በምክክሩ ሂደትና የሚቀርቡ መፍትሔዎች ትግበራ ላይ ጥርጣሬ ኖሯቸው ወደኋላ ሊሉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ስለሀገር በሚሰራ ስራ ላይ ‘አትሳተፉም’ ቢባል እንኳን ታግሎ መሳተፍ ያስፈልጋል፡፡ በምክክሩ ሂደት አለመሳተፍ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡” ሲሉ በሂደቱ እየተሳተፉ የማይገኙ አካላት እንዲሳተፉ ኮሚሽነር ሙሉጌታ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
እስከአሁን ባለው ሂደት ኮሚሽኑ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎችና ከዳያስፖራዎች እንዲሁም በጥናት የአጀንዳ ሀሳቦችን በማሰባሰብ እያጠናቀቀ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ምክክር የሚደረግባቸው እጅግ መሰረታዊና ሀገራዊ ያለ መግባባት ምክንያት የሆኑ አጀንዳዎችን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክር ቤት ከሚደግፏቸው አካላት ጋር በመሆን ይለያሉ፡፡ ከዚህ አኳያ አጀንዳ ለመቅረፅ ባለሙያዎች የተሰበሰቡትን አጀንዳዎች እየተመለከቱ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
አጀንዳው ተቀርፆ ለህዝብ ይፋ ከተደረገ በኋላ የሚቀጥለው ተግባር ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ማካሄድ ሲሆን በጉባኤው ከ4 ሺህ 500 በላይ ተወካዮች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች፣ ሊሂቃንና ፖለቲከኞችን ያካተተ እንደሚሆን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ሰብሳቢ መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) በቅርቡ ለመገናኛ ብዙሃን እንደገለፁት፣ ኮሚሽኑ ስራውን እንዲያጠናቅቅ በአዋጅ የተፈቀደለት ጊዜ ከአምስት ወይም ስድስት ወር የማይበልጥ ሲሆን በቀረው ጊዜ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ተካሂዶ በምክክሩ የሚቀርቡ ምክረ ሀሳቦችን በማቅረብ ስራውን አጠናቅቆ ይጨርሳል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ምክንያቱም ምክክር ይጀመራል እንጂ አያልቅም፤ በአንዳንድ አጀንዳዎች ላይ መግባባት ለመድረስ ወራትን ብቻም ሳይሆን ዓመታትን ሊወስድ ይችላል፡፡ የሀገረ መንግስት ግንባታው ላይ የሚታዩ የበዙ ችግሮችን በትክክልና በምክንያት በሚገባ በመወያየት ወደ አንድ ደረጃ ለማድረስ ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ በአዲስ አበባ የቦሌ አራብሣ ነዋሪ አቶ ታደሰ ጸጋዬ ለዝግጅት ክፍላችን እንደተናገሩት፣ እንደሀገር ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን ከውይይት ይልቅ ሀይልን በመጠቀም ለመፍታት ስንሞክር ቆይተናል፡፡ ይህ አካሄድ የምንፈልገውን ቀጣይነት ያለው ሰላም፣ መረጋጋትና ልማት አላመጣልንም። የማያግባቡ ችግሮችን ለመፍታት ሀገራዊ ምክክሩ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ያነሱት አቶ ታደሰ፣ ሁላችንም የአንድ ሀገር ወንድማማችና እህትማማች ህዝቦች እንደመሆናችን ልዩነቶቻችንን በምክክር ለመፍታት መስራት እንዳለብን ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ስድስት ኪሎ አካባቢ ያገኘናቸው በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ጎለልቻ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ሼህ መሀመድ ሼህ ሀቢብ ኢትዮጵያ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ የተለያዩ ልማቶችን በማጠናቀቅ በለውጥ ጎዳና ውስጥ ትገኛለች፡፡ በልማቱ እየተገኘ ያለው ውጤት አስደሳች ነው፡፡ ይህንን ድል ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት በማምጣት ለመድገም አለመግባባቶችን ወደ ጠረጴዛ በማምጣት በውይይትና በምክክር መፍታትን መለማመድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ሼህ መሀመድ፤ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ በተከናወነው የአጀንዳ ሀሳብ ማሰባሰቢያ መድረክ የሚኖሩበትን ወረዳ ወክለው መሳተፋቸውንና በሀገራችን ለሰላም እጦት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን ማንሳታቸውንም አክለዋል፡፡
ኮሚሽነር ሙሉጌታ እንደተናገሩት ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን መንግስትና ህዝብ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡ ኮሚሽኑ በተንቀሳቀሰባቸው አካባቢዎች ሁሉ ህዝቡ ያለምንም ገደብ በነፃነት ሀሳቡን በመስጠት እየተሳተፈ ይገኛል፡፡ ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች ሳይቀር የፀጥታ ስጋት ሳይበግረው በሂደቱ ከፍተኛ ተሳትፎ አድርጓል፤ ለዚህም ምስጋና ይገባዋል፡፡ ህዝቡ የሂደቱ ባለቤት እንደመሆኑ በቀጣይም የምክክሩን ሁኔታ በመከታተል፣ የሚጎድለውን በማመላከትና እንዲሟላ በማድረግ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ መገናኛ ብዙሃንም ስለሂደቱ መረጃ ለህብረተሰቡ በመስጠትና በማስተማር፣ ክፍተቶችን በመጠቆምና መፍትሔዎችን በማመላከት የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በስንታየሁ ምትኩ