ብቁ የቱሪዝም ባለሙያዎችን ለማፋራት ምን እየተሰራ ነው?

You are currently viewing ብቁ የቱሪዝም ባለሙያዎችን ለማፋራት ምን እየተሰራ ነው?



“በቱሪዝም ዘርፍ በሙያው የሰለጠነ የሰው ኃይል ከማፍራት አንፃር በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚታየው ዋና ጉድለት ‘ነፍስ እና ስጋ ያለው ስልጠና’ የመስጠት ክፍተት ነው”
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም እና የሆቴል ማኔጅመንት መምህር ደመቀ ክብሩ

ቱሪዝም ለኢኮኖሚ እድገት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለባህል ልውውጥ መሰረት ነው። የአንድ አገር የቱሪዝም ዘርፍ ስኬት በዋናነት የሚመጣው ደግሞ በዘርፉ ባለው የሰው ሀብት ብቃት ነው። ስለዚህ በቱሪዝም ልማት ውስጥ ሙያዊ አቅም እና ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች ለማፍራት እና በኢንዱስትሪው ውስጥ ያላቸውን ቁልፍ አስተዋፅኦ እንዲወጡ ማድረግ ይገባል። ለዚህ ደግሞ አገራት የሚጠበቅባቸውን ሥራ መፈፀም ይኖርባቸዋል፡፡

ለዓለም ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደርጋል፤ ቱሪዝም፡፡ በጎርጎሮሳዊያን ዘመን ቀመር 2024 መጨረሻ ላይ የወጣው የWorld Travel & Tourism Council (WTTC) ሪፖርት እንደሚያመላክተው፤ ከዓለም አቀፉ የአገር ውስጥ ምርት 10 ከመቶ የሚሸፍነው ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘው ነው፡፡ በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ አስር ሥራዎች አንዱን የሚሸፍነው ይኸው ዘርፍ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት ደግሞ  ዘርፉ ብዙ ትርጉም ያለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት የሚያግዙ በርካታ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ሰው ሠራሽ ፀጋዎች አሏት፡፡ እነዚህን በአግባቡ መጠቀም ከቻለች ቱሪዝም የኢኮኖሚ ብዝሃነት እና የውጭ ምንዛሪ ገቢ እድልን የመፍጠር አቅሙ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህንን አቅም ለመጠቀም ደግሞ፤ የአገልግሎት ጥራትን የሚያረጋግጡ፣ መዳረሻዎችን በብቃት የሚያስተዳድሩ እና የጎብኝዎችን እርካታ የሚያጎለብቱ ብቁና በቂ ባለሙያዎች ማፍራት ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፉን አንዱ የኢኮኖሚ ምሰሶ አድርጋ ለመጠቀም እየሠራች ያለችው ሥራ ውጤታማ እንዲሆን በሰው ሃብት ልማት ላይ በትኩረት መሠራት እንደሚገባው ያነጋገርናቸው የዘርፉ ምሁራን ያረጋግጣሉ፡፡ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም እና የሆቴል ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ኃላፊ እና መምህር የሆኑት ደመቀ ክብሩ በሰጡት ሃሳብ እንደጠቆሙት፤ “ማንኛውም ነገር ትርጉም የሚኖረውም የሚያጣውም በሰው ነው፡፡ ቱሪዝም ለሰው፣ በሰው የሚከወን ተግባር ነው። የቱሪዝም ውጤታማነት የሚወሰነው በሙያው በሰለጠነና ብቃት ባለው በሰው ኃይል ነው። ምክንያቱም በሙያው የሰለጠኑ ሰዎች ዘርፉን ይፈጥሩታል፣ ያስተዳድሩታል፣ ያሳድጉታል። ሥራውን በዕቅድ ይመሩታል።

ይህንን ሃሳብ የሚደግፍ ምሁራዊ ዕይታቸውን ያካፈሉት ከፍተኛ የቱሪዝም ተመራማሪ እና መምህር አያሌው ሲሳይ(ዶ/ር) በበኩላቸው ጉዳዩን ድግስ ካዘጋጀ እና ወደ ድግሱ ከተጠሩ እንግዶች ጋር በማያያዝ በተምሳሌት እንዲህ ገልጸወታል፤ “እንግዳ ጠርተህ በደንብ የሚያስተናግድ ሰው ከሌለ ውጤቱ ጉዳት ነው፡፡ እንግዳ የጠራ አካል በደንብ መዘጋጀት አለበት። ምንም ያክል የተሟላ ድግስ ቢያሰናዳም ያንን በአግባቡ የሚያስተናግድ ሰው ከሌለው በእንግዶቹ የሚደርሰው አሉታዊ ስሜትና እሱን ተከትሎ የሚከሰተው ጉዳት ከፍተኛ ነው። ስለዚህ እንግዶችን ወይም ጎብኝዎችን የሚጠራ የቱሪዝም ሥፍራ የተሟላ መስተንግዶ ለመስጠት ሁሌም የተዘጋጀ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ በሙያና በዕውቀት የደረጁ ሙያተኞች ያስፈልጋሉ። እነዚህ ሙያተኞች በስነምግባራቸው እና በአለባበሳቸው የጎብኚዎችን ልብና ቀልብ የሚስቡ ሊሆኑ ይገባል፡፡”

ብቃት ያላቸው ባለሙያዎች የአገራት የቱሪዝም ዘርፍ የጀርባ አጥንት ናቸው። ከፖሊሲ ቀረጻ እስከ አገልግሎት አሰጣጥ ድረስ በሁሉም ደረጃዎች አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሙያተኞች የአንድን አገር የቱሪዝም መስህብ፣ መልካም ስም እና ዘላቂነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። በቱሪዝም ዘርፍ ከሚያስፈልጉ የሙያ መስኮች መካከል ዋና ዋናዎቹ የሆቴል አስተዳደር፣ የማርኬቲንግ፣ የታሪክ፣ የሰው ሀብት አስተዳደር፣ የማህበረሰብ ሣይንስ

መሆናቸውን የጠቆሙት በጅማ ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም እና የሆቴል ማኔጅመንት መምህሩ ደመቀ ናቸው፡፡

እንደሳቸው ገለጻ፤ የቱሪዝም እና የሆቴል አገልግሎት የማይነጣጠሉ ናቸው። ስለዚህ በሆቴል አስተዳደር እና በቱሪዝም አስተዳደር የሰለጠነ ሙያተኛ ያስፈልጋል። ያሉንን የቱሪዝም ሃብቶች ለጎብኚዎች ማድረስ የምንችለው ስናስተዋውቀው ነው። ለዚህ ደግሞ በማርኬቲንግ የሰለጠነ ሙያተኛ ለኢንዱስትሪው ወሳኝ ነው። ከሰው ኃይል ቅጥር እስከ ስንብት ያለውን ሂደት የሚመራና የሚያስተዳድር የቱሪዝም አስተዳደር ሙያተኛም ያስፈልጋል። በተመሳሳይ፤ የቱሪዝም ሃብቶች በአብዛኛው ከታሪክ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያን፣ የአክሱም ሐውልት፣ የጀጎል ግንብ… ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ጠንካራ ግንኙነት አላቸው፡፡ የገዳ ሥርዓት፣ ጥምቀት፣ መስቀል፣ ጨንባላላ …

ውስጥም ታሪክ አለ፡፡ እነዚህን የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶችን ጨምሮ የኢትዮጵያን የቱሪዝም መዳረሻዎች በአግባቡ ለማስጎብኘት በታሪክ ዕውቀት ያለው ሙያተኛ ማፍራት ይገባል። ባህልን ታሳቢ ያደረገ በማህበረሰብ ሣይንስ (Anthropology) የሰለጠነ፣ ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለመስጠት በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ የሰለጠነ ሙያተኛ ያስፈልጋል። በአስጎብኚነት(Tour and Traveling)፣ በምግብ ዝግጅት፣ በመጠጥ፣ በእንግዳ አቀባባል፣ በቤት አያያዝ፣ በንፅህና አጠባበቅ፣ በቋንቋ የሰለጠኑ ሙያተኞችን ማፍራት ይገባል፡፡ 

“የቱሪዝም ዘርፍ የማይነካው ሴክተር የለም፡፡ ከከፍተኛው የመንግስት መዋቅር ጀምሮ፣ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ ሆቴልና

ሪዞርቶች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፣ የትምህርትና ስልጠና ተቋማት የመሳሰሉት ከቱሪዝሙ ዘርፍ ጋር በቀጥታ ግንኙነት አላቸው። በእነዚህ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ሙያተኞች በዕውቀት፣ በክህሎት እና በስነ ምግባር የበቁ መሆን አለባቸው” የሚሉት አያሌው ሲሳይ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ “በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ያሉ ሙያተኞች ስለሚጎበኘው አካባቢ በሚገባ የሚገልጡ፣ መንገድን በአግባቡ የሚያመላክቱ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በስፋት እየለሙ ያሉት የቱሪዝም መዳረሻዎች ውጤታማ እንዲሆኑ በዘርፉ ብቁና በቂ ሙያተኞች እንደሚያስፈለጉም አንስተዋል። በአሁኑ ወቅት እንደአገር እየተሠራ ያለው ይህንን ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም ገልጸው፤ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት እና የሰው ሀብት ልማት ተያይዘው የሚሄዱ ተግባራት ናቸው ብለዋል፡፡

በቱሪዝም ዘርፍ በዕውቀትና ክህሎት የዳበሩ ሙያተኞችን በማፍራት ረገድ እንደአገር ከዓመት ዓመት መሻሻሎች እየታዩ ስለመሆናቸው ያነጋገርናቸው ምሁራን ይመሰክራሉ፡፡ መንግስት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠቱ፤ ለቱሪዝሙ ዘርፍ ራሱን የቻለ የትምህርትና ስልጠና መርሃግብር(ካሪኩለም) ተዘጋጅቶለታል። አሁን ላይ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት(ዩኒቨርሲቲ እና ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛዎች) በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በአምስት ዓመቱ ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድን ጥቅል ውጤት በጥናት ለማረጋገጥና በገለልተኛ አካል ለማስጠናት ዕቅድ መያዙን የረጅም እና የአጭር ጊዜ ስልጠናዎች በስፋት እና በብዛት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም እና የሆቴል ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ኃላፊ እና መምህር የሆኑት ደመቀ ክብሩ የሚሠሩበትን ዩኒቨርሲቲ ተሞክሮ በማንሳት የቱሪዝምን ዘርፍ በሙያተኞች ለመደገፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየሠሩት ስላለው ተግባር አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ እሳቸው እንዳብራሩት፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንደአገር ሦስት መሰረታዊ ተልዕኮዎችን ይዘው ነው የሚሠሩት፡፡ እነዚህም ተልዕኮዎች ማስተማር፣ ምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎት ናቸው፡፡ የጅማ ዩኒቨርሲቲም እነዚህን ተልዕኮዎች ለማሳካት እየሠራ ይገኛል፡፡ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ያተኮሩ የሙያ መስኮችን ከ2007 የትምህርት ዘመን ጀምሮ በመጀመሪያ ድግሪ እና በሁለተኛ ድግሪ ለሰልጣኞች እየሰጠ ሙያተኞችን እያፈራ ይገኛል፡፡ ወደፊትም ይህንን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በዘርፉ ለአገራቸው የሚጠቅሙ ሙያተኞችን ማፍራታችንን እንቀጥላለን፡፡ ተማሪዎች ሲመረቁ የተለያዩ የጥናት እና ምርምር ሥራዎችን ይሠራሉ። ደረጃቸውን የጠበቁ የጥናትና ምርምር ጽሑፎች እንዲታተሙና ለአንባቢያን እንዲደርሱ ይደረጋል፡፡ በመምህራንም ጥናቶች እና ፕሮጀክቶች ይሠራሉ፡፡ Development team training program DTTP የተሰኘ መርሃግብር እንደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ይህ መርሃግብር የሁለተኛ ድግሪ ተማሪዎች በመጨረሻ የመመረቂያ ዓመታቸው ላይ በቡድን በመሆን የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር በመለየት በጥናት ላይ የተመሰረተ ተግባራዊ  መፍትሄ የሚሰጡበት አማራጭ ነው፡፡ በተቻለ አቅም ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ላሉ ሙያተኞች በዩኒቨርሲቲው ስልጠና ይሰጣል፡፡ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከሆቴሎች ጋር በቅርበት እና በቅንጅት ይሠራል፡፡

“በቱሪዝም ዘርፍ በሙያው የሰለጠነ የሰው ኃይል ከማፍራት አንፃር በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚታየው ዋና ጉድለት ʻነፍስ እና ስጋ ያለው ስልጠና’ የመስጠት ክፍተት ነው” የሚሉት በጅማ ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም እና የሆቴል ማኔጅመንት መምህሩ ደመቀ፤ “ተማሪዎች ወይም ሙያተኞች በንድፈ ሃሳብ የወሰዱትን ትምህርትና ስልጠና ወደ ነባራዊው ዓለም ወስዶ የመተግበር ክፍተት አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ አብዛኞቹ ትምህርትና ስልጠናዎች በንድፈ ሃሳብ ላይ ብቻ ያተኮሩ መሆናቸው ነው። ስለዚህ ስልጠናዎች የንድፈ ሃሳብ እና የተግባር ቅንጅት ያለባቸው መሆን ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ የሆቴልና ቱሪዝም ስልጠና የሚሰጡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በማሰልጠኛዎቻቸው ውስጥ በንድፈ ሃሳብ የተማሩትን የሚተገብሩበት ሆቴሎች ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር ጅምሮች አሉ፡፡ የንድፈ ሃሳብና የተግባር መቀናጀት ስልጠናው ነፍስና ስጋው የተጣመረ ይሆናል፡፡ ስልጠናዎች በንድፈሃሳብም በተግባርም የተደገፉ መሆን አለባቸው፡፡ ሙያተኛው ስላሉን ሃብቶች፣ ስለሚሠራው ሥራ በቂ ዕውትና ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል፡፡ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ተቋማት የተደራጁና የበቁ መሆን አለባቸው። ንድፈ ሃሳብን ከተግባር ጋር አዋህደው የሚተገብሩ ሊሆኑ ይገባል። አሰልጣኞችም ራሳቸውን በዕውቀት እና በክህሎት እያሳደጉ ሊሄዱ ይገባል” በማለት አብራርተዋል፡፡

እንደ አገር በቱሪዝም ዘርፍ የተካኑ ባለሙያዎችን ማፍራት እና ወደ ሥራ ማሰማራት ይዟቸው የሚመጣ በርካታ ጥቅሞች እንዳሉ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በጎርጎሮሳዊያን የዘመን ቀመር 2024 “Tourism for Development in Africa: Unlocking Inclusive Growth” በሚል ርዕስ የዓለም ባንክ ባወጣው ሰነድ ላይ እንዳስነበበው የቱሪዝሙን ዘርፍ በሙያው በተካኑና በበቁ ሙያተኞች መምራትና ማንቀሳቀስ ለአገራት ብዙ ጠቀሜታን ያስገኛል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ፡- የኢኮኖሚ እድገት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የውጭ ምንዛሪ ገቢ፣ ለአገር የገጽታ ግንባታ እና ኢንቨስትመንት መሻሻል የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍ ያለ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡

ቱሪዝም በሰዎች ላይ ያተኮረ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ስኬቱም ውድቀቱም በሰዎች ችሎታ፣ ሙያዊ ብቃት እና ፈጠራ ላይ የተመሰረተ ነው። የቱሪዝም ዘርፉ ከያዘው ፀጋ ስፋትና ጥልቀት እንዲሁም ከኢኮኖሚ መሰረታዊ ምሰሶዎች እንደአንዱ አድርገው ለወሰዱ ለኢትዮጵያ እና ለሌሎች ታዳጊ አገሮች የሰለጠነ የሰው ኃይል መገንባት ቅንጦት ሳይሆን የግድ ነው። ስለሆነም በዕውቀትና በክህሎት የላቁ፣ በመጠንም በቂ የሆኑ የቱሪዝም ባለሙያዎችን ለማፍራት የትምህርትና ስልጠና ተቋማትን ማጠናከር፣ኢንዱስትሪ-የአካዳሚክ ትብብርን መፍጠር የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት፣ በሥራ ላይ ላሉ ሙያተኞች ተከታታይነት ያለው የሥራ ላይ ስልጠና መስጠት፣ ለኢንዱስትሪው የፖሊሲ እና ተቋማዊ ድጋፍ ማድረግ ይገባል፡፡

በደረጀ ታደሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review