የመዲናዋ ኪነ ጥበባዊ መረጃዎች

You are currently viewing የመዲናዋ ኪነ ጥበባዊ መረጃዎች

ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ የተለያዩ የኪነ ጥበብ ስራዎች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም መሰል መሰናዶዎች ይቀርባሉ፡፡ ከእነዚህ  መካከል የመጻሕፍት ምረቃ፣ የሥዕል አውደ ርዕይ፣ ጥበባዊ ውይይቶችና የቴአትር መርሃ ግብሮች ይገኙበታል። ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡ 

መጻሕፍት

የቀድሞ ሙዚቀኛና የአሁኗ ዘማሪት ዘሪቱ ከበደ ከወር በፊት ‘ከልጅነት እስከ ልጅነት’ በሚል ርዕስ የራሷን ግለ ታሪክ መጽሐፍ እንዳሳተመች ይታወቃል። ይኸን መጽሐፍ መነሻ በማድረግ ዛሬ ከ8፡00 ሰዓት ጀምሮ በዛጎል የመጻሕፍት ባንክ አሰናጅነት ውይይት ይደረጋል። የውይይቱ አዘጋጅና አቅራቢ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ሲሆን የመጽሐፉ ደራሲ ዘሪቱ ከበደ ተጋባዥ እንግዳ በመሆን በመድረኩ ትገኛለች፡፡ የውይይቱ ቦታው የካቶሊክ ኪዳነ ምሕረት ትምህርት ቤት ፊት ለፊት፣ ባማ ሕንጻ አጠገብ በሚገኘው ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (FSS.) አዳራሽ ውስጥ ነው፡፡

በሌላ መረጃ ‘የተረክ ኃይል’ (The Power of Myth) በሚል ርዕስ ውይይት ይደረጋል፡፡ በዐውደ ፋጎስ የውይይት ክበብ የተሰናዳው ይሄ መሰናዶ ነገ ከቀኑ 8:00 ሰዓት ጀምሮ ይደረጋል፡፡ የውይይቱን መነሻ ጽሑፍ የሚያቀርበው መምህር ፀጋው ማሞ ሲሆን፣ ውይይቱ የሚካሄድበት ቦታ ደግሞ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት (ወመዘክር) አዳራሽ ውስጥ ነው።

ሙዚቃ

የድምፃዊ ሀይሉ አመርጋ ‘አሁን’  የተሰኘው አዲስ የሙዚቃ አልበም በመደመጥ ላይ ይገኛል፡፡ ሙዚቀኛው በራሱ የዩቲዩብ ቻናል እና በዓለም አቀፍ የሙዚቃ ማሰራጫ መተግበሪያዎች በኩል ነው ለሙዚቃ አፍቃሪያን ያቀረበው። በአልበም ስራው ላይ ሚካኤል ሀይሉ (ሚኪ ጃኖ)፣

ብሩክ አፈወርቅ፣ በረከት ተስፋአፅቂ፣ ኤርሚያስ ሞላ፣ አበጋዝ ክብረወርቅ ሽዎታ እና ሮቤል ዳኜ፣

አክሊሉ ገ/መድህንና ወንደሰን ይሁብ በግጥም፣ በዜማና በሙዚቃ ቅንብር ተሳትፈዋል። ሀይሉ አመርጋ የታዋቂው የጃኖ ባንድ መስራች ከሆኑ ድምጻውያን መካከል አንዱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ቀደም በባንዱ አማካኝነት ተወዳጅ ሙዚቃዎችን ለአድማጭ በማቅረብ ዕውቅና ያገኘ ሙዚቀኛም ነው፡፡ ይሄን የሙዚቃ አልበም ግን ከባንዱ ውጪ ለብቻው የሰራው የመጀመሪያ የሙዚቃ አልበሙ ነው፡፡

ሥዕል

‘አብሮነት’ የሥዕል አውደ ርዕይ የፊታችን ረዕቡ ህዳር 3 ቀን 2018 ዓ.ም በፈንደቃ የባህል ማዕከል ውስጥ በይፋ ይከፈታል፡፡ አውደ ርዕዩ ሰዓሊያን በቡድን ሆነው ያሰናዱትና አብሮነትና ህብረትን የሚያሳዩ የሥዕል ስራዎች የሚቀርቡበት ነው፡፡ በአውደ ርዕዩ ላይ የሥዕል ሥራዎቻቸውን ከሚያቀርቡ መካከል

ብሩ ወርቁ፣ ያሬድ ወንድወሰንና ዘውዱ ገብረሚካኤል ይገኙበታል፡፡ የስዕል አውደ ርዕዩ እስከ መጪው ህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ለተመልካች ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡

የቴአትር መርሃግብር

በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና አሁድ የተለያዩ ቴአትሮች ይታያሉ፡፡ ቅዳሜ 8:30 ሰዓት 12ቱ እንግዶች፣ 11፡30 ሰዓት ደግሞ ባሎችና ሚስቶች እንዲሁም እሁድ በ8፡30 ሰዓት ንጉሥ አርማህ፣ እንዲሁም 11፡30 ሰዓት እምዬ ብረቷ  የተሰኙ ቴአትሮች በብሔራዊ ቴአትር ይታያሉ። በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ደግሞ እሁድ በ8:00 ሰዓት በዓሉ ግርማ ቤርሙዳ የተሰኘው ቴአትር ይታያል፡፡

በተጨማሪም ማክሰኞ በ11፡30 ሰዓት ሶስቱ አይጦች፣ ረዕቡ በ11፡30 ሰዓት የቅርብ ሩቅ፣ ሐሙስ 11:30 ሰዓት ሸምጋይ እንዲሁም አርብ በ11፡30 ሰዓት የሕይወት ታሪክ በብሔራዊ ቴአትር ለጥበብ አፍቃሪያን ለዕይታ ይቀርባሉ፡፡

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review