የከተማ ግብርና አብነቶች

You are currently viewing የከተማ ግብርና አብነቶች

የሚመረተው የጓሮ አትክልት ትኩስና ንፁህ በመሆኑ ለጤናችን ተመራጭ ነው፡፡

የከተማ ግብርና በሰፊም ይሁን በአነስተኛ ቦታ፣ ለምግብነትና ለገቢ ምንጭነት ሊውሉ የሚችሉ እፅዋትን የማልማት፣ እንስሳትን የማርባት፣ የግብርና ምርት ውጤቶችን ከማምረት ባሻገር የማቀነባበር እና ለተጠቃሚዎች የማቅረብ ስራን የሚያካትት ነው። ብዙዎች በዚህ ዘርፍ በመሰማራት ተጠቃሚ በመሆን ላይ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ትጉህ፣ መስራት ከማይታክታቸው ከራሳቸው ይልቅ የማህበረሰቡን ጥቅም ካስቀደሙ ጠንካራ አባቶች አቶ ጥላሁን ያለው አንዱ ናቸው፡፡

አቶ ጥላሁን የከተማ ግብርናን የጀመሩት በመኖሪያ ቤታቸው ቅጥር ግቢ ውስጥ  አጥራቸው አጠገብ ጎመን፣ ቆስጣ፣ ሰላጣና መሰል የጓሮ አትክልቶችን በማልማት ነበር። ስራ ወዳድነታቸው፣ ጠንካራና ታታሪነታቸው እንዲሁም ከራሳቸው አልፈው ማህበረሰቡንም ይጠቅማሉ በማለት የጉለሌ ክፍለ ከተማ እና የወረዳ 10 አስተዳደር 700 ካሬ  ቦታ ላይ የከተማ ግብርና የሚሰሩበትን እንዲያለሙ እንደሰጧቸው ነግረውናል። ቦታው ሲሰጣቸው የቆሻሻ መድፊያ የነበረ በመሆኑ ለስራው ምቹ ለማድረግ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት አስተካክለውት  ስራ ጀምረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የዶሮ እርባታ እና የጓሮ አትክልት ስራዎችን በስፋት እየሰሩበት ነው፡፡ 

በከተማ ግብርናው ተግባር የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን አምርቶ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ዓላማቸው ያደረጉት አቶ ጥላሁን፤ ከሚያለሟቸው ልማቶች ለምግብነት ከሚያገለግሉ አትክልቶች መካከል ጎመን፣ ሰላጣ፣ ቀይ ስር፣ ስፒናች፣ ካሮት፣ ነጭ ሽንኩርት፣ በሶብላ፣ ኮሰረት፣ የስጋ መጥበሻ፣ ጤናዳም  የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሌሎች ከምግብነት ውጭ የወይን ተክል፣ ጌሾ፣ ቡና፣ እንሰትና መሰል ተክሎችን በቦታው ላይ እያለሙ ይገኛሉ፡፡

እንደ ጎመን፣ ቆስጣ እና ሰላጣ የመሳሰሉት የጓሮ አትክልቶች ለማህበረሰቡ ትኩስ፣ በመጠንም ውጭ ላይ ከሚሸጠው ብዛት ያለው እና ዋጋውም በግማሽ በሚቀንስ እንደሚሸጡ ገልፀው፤ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ትኩስ የጓሮ አትክልታቸው ተቋዳሽ እንዲሆኑ ለማድረግ  ለአንድ ግለሰብ ከአንድ እስር በላይ ጎመንም ይሁን ቆስጣ እንደማይሸጡ ነግረውናል፡፡

አትክልት ስለምወድ በመኖሪያ ቤቴ አጥር አጠገብ፣ በተለያዩ እቃዎች ላይ ሳይቀር ጎመን፣ ቆስጣ፣ ሰላጣ፣ ስፒናች እና የመሳሰሉትን የጓሮ አትክልቶች አለማለሁ፤ የራሴንም ፍጆታ እሸፍናለሁ የሚሉት አቶ ጥላሁን፤ ብዙ ወጭ አውጥቼበት የምሰራበት ይህ ቦታ ሰዎች ጥቅም ላይ የማይውሉ የሚመስሏቸው ነገሮች ጥቅም ላይ ሲውል እያዩ እንዲማሩበት፣ ትኩስና ጤናማ ምግብ ማግኘት እንዲችሉ እንዲሁም ጊዜያቸውን ያለ አግባብ የሚያባክኑና አልባሌ ቦታ የሚያሳልፉ የማህበረሰብ ክፍሎች በሚኖሩበት ቦታ ማልማት እንዲችሉ ለማስተማር ያግዛል ይላሉ፡፡  

በአሁኑ ወቅት የክረምቱ በረዶ የጓሮ አትክልታቸውን አበላሽቶባቸው ለገበያ የሚቀርብ የጓሮ አትክልት ባይኖርም ከዚህ በፊት በቀን ከ200 እስከ 300 የሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ተሰልፈው ይገዟቸው እንደነበር አስታውሰው “ይህ ለእኔ ደስታ ነው፤ ከዚህ በላይ የሚያስደስተኝ ምንም ነገር የለም። ለምግብ የደረሰውን የጓሮ አትክልት ከመሸጥ ባለፈ ሰዎች በመኖሪያ ቤታቸው እቃ ላይም ቢሆን እዲያለሙና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከምዘራው ዘር እሰጣቸዋለሁ” የሚሉት አቶ ጥላሁን ማህበረሰቡ ሲጠቀም የሚደሰቱ መሆናቸውን ነግረውናል፡፡

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚኖሩት የማህበረሰብ ክፍሎች ገንዘብ ጨምሬ እና መጠን ቀንሼ ከምሸጥ በተመጣጠነ ዋጋ ትኩስ አትክልት በማቅረብ ደስታዬን እመርጣለሁ የሚሉት አቶ ጥላሁን፤  በዶሮ እርባታ ስራው ላይ ወደፊት የገቢ ምንጭ ይሆናሉ በማለት 350 ዶሮዎችን እያረቡ ይገኛሉ፡፡ ምርት መስጠት የጀመሩት ዶሮዎች በቀን እስከ 150 እንቁላል ይጥላሉ፡፡  ወደፊትም የተሻለ ገቢ እንደሚያስገኙ ተስፋን ሰንቀው እየሰሩ እንደሚገኙ ነው የነገሩን፡፡

በመዲናዋ የተጀመረው የከተማ ግብርና ነዋሪዎች ከጓሯቸው አትክልትና ፍራፍሬዎችን እንዲሁም የወተት ተዋፅኦዎችን እንዲያገኙ እያደረገ ነው። እኔም ወደፊት እንቁላሉን በመሸጥ ተጠቃሚ የምሆንበት ጊዜ ሩቅ አይደለም።

አቶ ጥላሁን ከስራ ወዳድነታቸው፣ እንደ እሳቸው ሰዎችም እንዲሰሩ ለማበረታታት ሁሉም በየደጃፉ የጓሮ አትክልት አልምቶ ተጠቃሚ እንዲሆን ከመፈለጋቸው የተነሳ “አንድ ወር እና ሁለት ወር በኋላ ለእናንተ ጎመን አልሸጥም ደጃፋችሁ ላይ አልሙ ከእናንተ አልፎ ለሌሎችም ትተርፋላችሁ” ብለው መክረው እደንሚሸኟቸው ነግረውናል፡፡

የጓሮ አትክልት ማልማት የመንግስት ሰራተኞች ከስራ ሲመለሱ በተለይ ወንዶቹ ገንዘብና ጊዜያቸውን እንዳያባክኑ ከማገዙም በተጨማሪ ትኩስና ጤናው የተጠበቀ ተመጣጣኝ ምግብ እንዲመገቡ  ያደርጋቸዋል፡፡ የጓሮ አትክልት በተለያዩ ቆሻሻ ፍሳሾች ሳይሆን በንፁህ ውሃ ስለሚመረት፣ እንዲሁም  ወዲያውኑ ተቆርጦ ጥቅም ላይ ስለሚውል በሽታ አምጭ ሳይሆን በሽታ ተከላካይና ለጤና ወሳኝነት ያለው መሆኑን ከራሳቸው ተሞክሮ በመነሳት ይናገራሉ፡፡

የከተማ ግብርናውን ስራ ውጤታማ ለማድረግ ዋጋው እየጨመረ የመጣውን የዶሮዎች  መኖ ለራሳቸውም ሆነ ለሚፈልጉ ሌሎች አካላት  አምርተው ለማቅረብ እቅድ እንዳላቸው ገልፀው፤ ይህም ሲሆን ማህበረሰቡ በቅናሽ በመግዛት ዶሮ እርባታ ስራ ላይ እንዲሰማራ የሚያግዘው ነው የሚሆነው ይላሉ፡፡

በከተማ ግብርና ላይ እየታየ ያለው መሻሻልና ተሞክሮ የሚደነቅ ነው፤ መንግስት ለእያንዳንዱ ሰው ዶሮዎችን እየገዛ ሲሰጥና ተጠቃሚ ሲያደርግ እየተመለከትኩ ነው፡፡  ይህ ተግባር የአንድ ወቅት ስራ ብቻ ሳይሆን ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ባይ ነኝ ይላሉ፡፡

ለአቶ ጥላሁን የስራ ታታሪነትና ስራ ወዳድነት እንዲሁም ጤናማ የጓሮ አትክልቶችን አምርቶ ለማህበረሰቡ ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ወይዘሮ ብልጫ አምዲሁን ይመሰክራሉ፡፡ የሸጎሌ መንደር 7 አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮዋ፤ አቶ ጥላሁን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚሰሩ ናቸው። የሚመረተው የጓሮ አትክልት በሚደርስበት ወቅት በተመጣጠነ ዋጋ እና በመጠንም ገበያ ላይ ከሚሸጠው የተሻለ እገዛለሁ፡፡ ትኩስና ንፁህ በመሆኑ ለጤና ተመራጭ ነው፡፡  በዚህ ስራ ከተሰማሩ ጀምሮ የጓሮ አትክልቶቹ ሲደርሱ ተጠቃሚ ነኝ” ሲሉ ደስተኛ መሆናቸውን ነግረውናል፡፡ 

ከአቶ ጥላሁን የተማርኩት ሸጠው ገንዘብ ስለማግኘት ሳይሆን ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ መሆኑን እና ሰዎች በቤታቸው ተክለው እንዲጠቀሙ ማበረታታቸውን ነው ሲሉም በራሳቸው ለራሳቸው ማልማት እንዳለባቸው መማራቸውን ነው የነገሩን፡፡

ሌላኛው የአቶ ጥላሁንን የደረሰ የጓሮ አትክልት  ገዝተው ከሚጠቀሙ አካላት ውስጥ  አንዱ ነኝ የሚሉት  ደግሞ አቶ ኤሊያስ ገብረወልድ ናቸው፡፡ “እንክብካቤ ሲደረግለት የምመለከተውና ለእይታ የሚማርከው ጎመኑም ሆነ ቆስጣው እስከሚደርስ በጉጉት  ነው የምጠብቀው፤  በዋጋም ሆነ በመጠን ገበያ ላይ ከሚሸጠው ጋር ይለያያል። ጣዕሙም ቢሆን ጣፋጭ ነው፡፡ ገበያ ላይ ከ50 እስከ 60 ብር የሚሸጠውን አትክልት አቶ ጥላሁን ጋር የምንገዛው 30 ብር ነው” ሲሉ ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የነገሩን፡፡

ወረፋ ስለሚሆን ተሰልፌ መግዛት በማልችልበት ወቅት እንዲያስቀምጡልኝ ደውዬ እነግራቸዋለሁ የሚሉት አቶ ኤሊያስ፤ ከአቶ ጥላሁን ከራስ ይልቅ ሌሎችን ማስቀደም  ደስተኛ እንደሚያደርግ ተምሬያለሁ ይላሉ፡፡      

አቶ ጥላሁንን  በስራ የሚያግዛቸው ወጣት ብርሃኑ ባበይ “እኔ በሰለጠንኩት የዶሮ እርባታ እንክብካቤ መሰረት ዶሮዎችን የመንከባከብ ስራ እሰራለሁ። የሚያስፈልጋቸውን ምግብም ሆነ ውሃ እንዲሁም የፅዳት ስራዎችን አከናውናለሁ፡፡ ጊዜ ሲኖረኝም የጓሮ አትክልቱን በመንከባከብ አግዛለሁ፡፡ ትኩስ አትክልቶችን ከዚሁ እጠቀማለሁ፤ ስራ ያልነበረኝን ስራ እንዲኖረኝ አድርገውኛል፡፡ በስራቸውም ታታሪ በመሆናቸው እኔም ጠንክሬ እንድሰራ አቅም ሆነውኛል ሲል  ነው የአቶ ጥላሁንን ስራ ወዳድነት እንዲሁም ለማህበረሰቡ አሳቢነት የነገረን፡፡

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 አርሶ አደርና ከተማ  ግብርና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቸርነት ሽፈራው በበኩላቸው፤ ወረዳውና ክፍለ ከተማው ቦታ ሰጥቷቸው ከተማ ግብርናን በማልማት አቶ ጥላሁን ሞዴል መሆናቸውን አንስተው፤ አቶ ጥላሁን የከተማ ግብርናን ለመስራት ካላቸው ፍላጎትና ተነሳሽነት የመነጨ የቆሻሻ መጣያ የነበረውን ቦታ ብዙ ወጪ አውጥተው ለልማት አውለውታል። በዚህም ማህበረሰቡ ንፁህና ጤናው የተጠበቀ አትክልት እንዲያገኝ ሆኗል። በቅርብ ጊዜም እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በመግዛት ማህበረሰቡን የእንቁላል ተጠቃሚ እያደረጉ ይገኛሉ። ማህበረሰቡም እሳቸውን በማየት እየተነሳሳና እንቁላል ጣይ ዶሮዎች እንዲሰጡት እየጠየቀ ነው ይላሉ፡፡  

ሙያዊ ድጋፍ እና የዘር አቅርቦት ከመደገፍ ውጭ ሌሎች ነገሮችን ከራሳቸው በማውጣት እየሰሩ  ማህበረሰቡን በቅናሽ ዋጋ እና ትኩስ ምርቶችን በማቅረብ ተጠቃሚ እያደረጉ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ   ለወረዳውም ሞዴል  መሆን ችለዋል፡፡

እንደ ከተማ የሌማት ትሩፋትን  ተግባራዊ ለማድረግ ከመስከረም 1 እስከ ታህሳስ 30 2018 ዓ.ም የሚቆይ  ንቅናቄ እየተደረገ ይገኛል፡፡

በዘርፉ የተሰማሩ ተሳታፊዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ የተለያዩ የግንዛቤ ፈጠራ፣ ሙያዊ ድጋፍ፣  የዘር አቅርቦት  ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ ቸርነት ወደ ፊትም ትኩረት ተሰጥቶበት  እንደሚሰራ ነው የነገሩን፡፡  

በፋንታነሽ ተፈራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review