የወንዝ ዳርቻ ልማቱ ፍሬ

You are currently viewing የወንዝ ዳርቻ ልማቱ ፍሬ

 • በካይ ተብለው ከተለዩት የግለሰብ መኖሪያ ቤት እና የመንግስት ተቋማት መካከል ከ11 ሺህ 670 በላይ በሚሆኑት ብክለትን የማስቆም ስራ እንደተሰራ ተጠቁሟል

እምየ ኢትዮጵያ ይመርልሽ ሰብሉ

አውድማው ጎተራው ይሁንልሽ ሙሉ

በቸር ውሎ ይደር ጋራ ሸንተረርሽ ወንዛ ወንዝሽ ሁሉ

ያደግኩበት ወንዝሽ የተራጨሁበት

ክፉም አልስማ ክፉም አልይበት

ሰላም ደምኖ ሰላም ይዝነብበት

ኢትዮጵያ የብዙ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ስለመሆኗ ከላይ የተጠቀሰውን ጨምሮ በተለያየ ጊዜ ተዚሞላታል፤ ተነግሮላታል፡፡ ሀገሪቷ ከመልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ ጀምሮ የተለያዩ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ናት፡፡ ምቹ የአየር ጸባይ፣ ብርቅየ የዱር እንስሳትና አዕዋፍት፣ ዓመቱን ሙሉ የማይነጥፉ ወንዞች… ባለቤት ናት፡፡ ይሁን እንጂ ከከተሞች መስፋፋት፣ ከሕዝብ መጨመር ጋር በተያያዘ ተጠብቀው በቆዩና ለአካባቢያዊ ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ባላቸው የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል። ለጉዳት ሰለባ ከሆኑ የተፈጥሮ ሀብቶች መካከል ወንዞች ይጠቀሳሉ።  ደኖች እየተመነጠሩ ወደመኖሪያነት መቀየራቸውና የደኖች መመናመን ለወንዞች መድረቅ ተጽዕኖው ከፍተኛ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የከተሞች መስፋፋትም ወንዞች በበካይ ኬሚካሎች እንዲበከሉ የራሱን አሉታዊ አስተወጽኦ እያደረገ ነው፡፡ 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ በተለይም በአዲስ አበባ የወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት የከተማ ገጽታ ማሻሻያ አካል ሆኗል፡፡ በዚህም መነሻነት የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር እንደገና ለመወሰን ተፈጻሚ እያደረገው ባለው አዋጅ ቁጥር 84/2016 አንቀጽ 95 መሰረት “የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወንዞች ዳርቻ ልማት እና ብክለት መከላከል ደንብ ቁጥር 180/2017” በሚል ስያሜ አውጥቶ ወደ ተግባር ከተገባ ውሎ አድሯል፡፡ በዛሬው ዕትማችን የደንቡ ተፈፃሚነት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በተመለከተ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የአካባቢ ብክለት ጥናት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሙላቱ ወሰኑን በማነጋገር እንዲሁም ከደንቡ መሰረታዊ ነጥቦችን በማካተት በሚከተለው መልኩ ዳስሰነዋል፡፡

ከፍተኛ ባለሙያው አቶ ሙላቱ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጹት፤ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አደረጃጀት፣ ሥልጣንና ተግባርን ለመወሰን የወጣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 545/2016 አንቀጽ 2 (2) ላይ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተያያዙ መሰረታዊ ነጥቦች ተቀምጠዋል። በደንቡ ላይ እንደተመላከተው፤ “የአካባቢ ጥበቃ ማለት፡- የሰው ልጅን ጨምሮ የማንኛውም አካል ሕይወት እና እድገት የሚወስኑ የመሬት፣ የውሃ፣ የአየር፣ የአየር ንብረት ሥርዓት፣ ሌሎች የአካባቢ ሀብቶች፣ ክስተቶችና ሁኔታዎችን በመጠበቅ የአሁኑን ትውልድ ፍላጎት የማርካቱ ሂደት የመጪውን ትውልድ ዕድል ሳያሰናክል እንዲሟላ ማስቻል ነው” በማለት ይበይነዋል፡፡ ከዚህ ትርጉም መረዳት እንደሚቻለው የአሁኑ ትውልድ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም የመጪውን ትውልድ በተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም መብት በማይጎዳ መልኩ ሊሆን ይገባል። ይህንን ቁልፍ እሳቤ መተግበር የሚረዱ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች በተግባር ላይ ውለዋል። ከእነዚህ መካከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወንዞች ዳርቻ ልማት እና ብክለት መከላከል ደንብ ቁጥር 180/2016 አንዱ ነው፡፡

   የደንቡ አስፈላጊነት

በ2017 በጀት ዓመት ወጥቶ ወደ ሥራ የገባው የወንዞች ዳርቻ ልማት እና ብክለት መከላከል ደንብ ቁጥር 180/2017 የወጣበት ዓላማና አስፈላጊነት በተመለከተ የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የአካባቢ ብክለት ጥናት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሙላቱ፤ “የአካባቢ ብክለትን በመከላከል ከተማውን የተፈጥሮ ሚዛኑን ለመጠበቅ፣ ጽዱ፣ አረንጓዴና ምቹ ለማድረግ ነው። ለዚህም በከተማው ውስጥ የሚገኙ ወንዞችና ዳርቻዎቻቸው ንጹሕና ጤናማ አካባቢ እንዲሆኑ ማድረግ ቅድሚያ የተሰጠው ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በመዲናዋ በሚገኙ ወንዞችና የወንዝ ዳርቻዎች ልማት ላይ የመጣው ለውጥ ህያው ምስክር ነው” ብለዋል፡፡

የወንዞች ዳርቻ ልማት እና ብክለት መከላከል ደንብ ቁጥር 180/2017 ለአዲስ አበባ ከተማ ምን ያክል አስፈላጊ እንደሆነ የመጣውን ተጨባጭ ለውጥ መመልከት ይበቃል፡፡ የወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ የኮሪደር ልማት ውጤት የዚህን ደንብ ወሳኝነት በገሃድ ያሳያሉ፡፡ ምክንያቱም ደንቡ መሰረታዊ ጉዳዮችን መሬት እንዲነኩ ያስቻለ በመሆኑ ነው። በደንቡ የተካተቱ አንዳንድ ቃላት እና ሀረጋት ለዚህ ሁነኛ አስረጂ ናቸው።  ደንቡ፤ “የወንዝ ዳርቻ” የሚለውን፤ ለወንዝ ዳርቻ መጠበቂያ ቢያንስ ከወንዙ ጠርዝ ግራና ቀኝ ዝቅተኛው 30 ሜትር ሆኖ እንደአካባቢው ሁኔታ አስተዳደሩ በሚወስነው መሠረት ስፋቱ ሊጨምር የሚችል ሲሆን ለማንኛውም ዓይነት ግንባታ ወይም አገልግሎት እንዲውል የማይፈቀድ ቦታ እና በወንዙ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ሥፍራን እንደሚያጠቃልል ይደነግጋል።  “የወንዝና ወንዝ ዳርቻ ኮሪደር ልማት” የሚለውን ሀረግ ደግሞ፤ ከወንዙ ተፋሰስ መነሻ ጀምሮ የሥነ-ምህዳር ጥበቃ፣ አረንጓዴ ልማት፣ መዝናኛ ቦታዎችን እና ተያያዥ አገልግሎቶችን ከወንዙ ኩታ-ገጠም የሆኑ አካባቢዎች ማልማት ሆኖ ወሰኑና የመሬት አጠቃቀሙ በጥናት የሚወሰን መሆኑን ደንግጓል።

በተጨማሪ፤ “የወንዝ ብክለት” የከተማዋ ወንዞች ከማንኛውም ግለሰብ፤ መኖሪያ ቤት፣ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሚመነጩ የተለያዩ በካይ ነገሮች ምክንያት የወንዝን ተፈጥሯዊ ባህሪ መቀየርን የሚያመለክት መሆኑን ያብራራል፡፡  “የወንዝ ሥርዓተ-ምህዳር” ማለት ደግሞ፤ በወንዝና በወንዝ ዳርቻ ያሉ ማናቸውም ሕይወት ያላቸው ነገሮች ከራሳቸው ጋርም ሆነ ሕይወት ከሌላቸው ነገሮች እንዲሁም ከአካባቢያቸው ጋር የሚያደርጉትን ያልተቋረጠ ተፈጥሮአዊ መስተጋብር የሚያሳይ ሥርዓት እንደሆነ አስፍሯል፡፡

የወንዝና ወንዝ ዳርቻ ልማት በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር ህጎችን ዓላማ ያሳካል፡፡ የህገ-ወጥ ቆሻሻ አወጋገድን ያስቀራል፡፡ እንዲሁም ለዘላቂ የመሬት አጠቃቀም ድጋፍ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። የወንዝና ወንዝ ዳርቻ ልማት ለዘላቂ የመሬት አጠቃቀም ድጋፍ ሲባል የወንዝ ዳር ኮሪደር ልማት የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል የሚያስችሉ እፅዋትን ለመትከል፣ የግንባታ መዋቅሮችን ለማበጀት እና የውሃ ፍሰትን ለማስተካከል ይረዳል። ይህ በረጅም ጊዜ ለአፈርና ውሃ ሀብት ዘላቂ አስተዳደር ወሳኝ ነው። የአፈር መሸርሸርን መቆጣጠር የመሬት ጥራት እንዲጠበቅ ከማድረጉም በላይ፣ የወንዙን የውሃ ፍሰት መደበኛነት እንዲያገኝ ያግዛል፡፡ ይህም የመሬት ይዞታ ህጎችን በተዘዋዋሪ ይደግፋል።

የኮሪደር ልማቱን  የበለጠ ዘላቂነት ባለው መልኩ ተንከባክቦ ለመያዝ ፋይዳው የጎለ ከመሆኑም ባሻገር በከተማ  “ስማርት ከባቢ”  ለመፍጠር የወንዙን ንጽህና መጠበቅና ለተለያዩ  ስርዓተ ምህዳራዊ አገልግሎት እንዲውል ማድረግ ፋይዳው የጎላ ነው።

በተለያየ መንገድ ወንዙን ለሚበክሉ አካላት ማለትም የአምራች ተቋማት፣ የአገልግሎት ሰጭ፣ የግለሰብ መኖሪያ ቤት እና የመንግስት ተቋማት በድምሩ ለ17 ሺህ 516 የልየታ (Mapping) ስራ ተከናውኗል፡፡ እነዚህ የተለዩት ግለሰቦች እና የተለያዩ ተቋማት ችግሩን የሚያስወግዱበትን መንገድ እንዲያበጁ እየተደረገ ነው።

የወንዙን የብክለት ደረጃ በጥናትና በላቦራቶሪ በመለየት ረገድም ሰፊ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ የወንዙን የብክለት ምንጮች ለመቀነስ በከተማው የፍሳሽ ማጣሪያ በመገንባት፣ ከወንዝ የተገናኘ ቱቦ በመቁረጥ፣ የፍሳሽ ሴፕቲክ ታንክ (ፍሳሽ እስከሚወገድ ድረስ በጊዜያዊነት የሚጠራቀምበት) በማዘጋጀት እና በቋሚና በሳይንሳዊ የማስመጠጫ ስርዓት በማከናወን ከየካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም እስከ መስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በካይ ተብለው ልየታ ከተደረገባቸው 17 ሺህ 516 የግለሰብ መኖሪያ ቤት እና የመንግስት ተቋማት መካከል ከ11 ሺህ 670 በላይ በሚሆኑት ብክለትን የማስቆም ስራ ተሰርቷል።

በለይላ መሀመድ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review