አዲስ አበባ የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ እና የአፍሪካ ህብረት ዋና መስሪያ ቤት መቀመጫ ናት፤ ለበርካታ ዓመታት ይህን ክብሯን በማይመጥን ልክ የተለያዩ ችግሮች ተጋርጠውባት ቆይታለች፤ ይህን ችግር ለመፍታት ቀላል የማይባሉ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ በተለይ በኮሪደር እና በወንዝ ዳርቻ ልማት እንዲሁም በግዙፍ ሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሳቢያ ስሟንና ክብሯን ወደሚመጥን ደረጃ ከፍ እንድትል ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ ጥናቶችና ምርምሮች የተደገፉ ስራዎችን መስራትም ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡
ከተማዋን በዘላቂ እድገት ለመምራት በተለያዩ ዘርፎች ጥናቶች እና ምርምሮችን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ጥርጥር የለውም። የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ የተቋቋመበት ዋና ዓላማም ይኸው ነው፡፡ ይህ ተቋም በዋናነት የስልጠና፣ የማማከር፣ የጥናትና ምርምር አገልግሎቶችን ይሰጣል።
በአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ የእቅድ ዝግጅትና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ጉራራ እንደሚሉት አካዳሚው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የከተማዋን ችግሮች በዋናነት የሚፈቱ በስራ እድል ፈጠራ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በርካታ የስልጠና፣ የምርምርና የማማከር አገልግሎቶች እየሰጠ ይገኛል፡፡
በተለይ የከተማ አስተዳደሩ ሪፎርም ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ በአዋጅ ቁጥር 84/2016 በተለየ መልኩ ተልዕኮ ተሰጥቶታል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ዋና ተልዕኮውም በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ የሚገኙ በመንግስትና በግል ተቋማት ለሚሰሩ አመራሮችና ባለሙያዎች በጥናትና ምርምር ግኝት ላይ የተመሰረተ ስልጠና በመስጠት ማማከርና የማህበረሰብ አገልግሎት በመስጠት የመፈፀም አቅማቸውን ማሳደግ ነው ብለዋል፡፡
ይህን መነሻ በማድረግም በ2017 ዓ.ም በተለይ ከስልጠና፣ ከማማከር፣ ከጥናትና ምርምር ስራዎች አንፃር በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ በአካዳሚው ስልጠና ላይ ጥናትና ምርምር ላይ የከተማ አመራር ልማት ዳይሬክቶሬት፣ የስራ አመራር ልማት ዳይሬክቶሬት፣ የጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት እና የማማከርና የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የተሰኙ አራት ዘርፎች አሉ፡፡
የስልጠና መርሃ ግብሮችም ለተሿሚ አመራሮች፣ ለዳይሬክተሮች፣ ለቡድን መሪዎች እና ባለሙያዎች ተብለው የሚከናወኑ ሲሆን፣ በዚህ መሰረት ባለፈው በጀት ዓመት በተለይ የከተማ አመራር ልማት ዳይሬክቶሬት በከተማዋ ላሉ 5 ሺህ ተሿሚ አመራሮች ስልጠና ለመስጠት አቅዶ 5 ሺህ 689 አሰልጥኗል፤ በተመሳሳይ 5 ሺህ 834 ዳይሬክተሮች እና ቡድን መሪዎችን ለማሰልጠን አቅዶ 5 ሺህ 343 ማሰልጠን ችሏል፡፡ በተጨማሪም 2 ሺህ 708 ባለሙያዎችን ለማሰልጠን አቅዶ 2 ሺህ 683 በማሰልጠን በአጠቃላይ በሁለቱ ዳይሬክቶሬቶች 13 ሺህ 542 ለሚጠጉ ከተሿሚ አመራር አስከ ባለሙያ ላሉ ስልጠና ለመስጠት አቅዶ 13 ሺህ 715 በማሰልጠን የእቅዱን 101 በመቶ ማከናወን ችሏል፡፡
ከጥናትና ምርምር ጋር ተያይዞም 14 ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ለመስራት ታቅዶ 16 የተከናወነበት፣ ከማማከር አገልግሎት ጋርም ተያይዞ 6 የማማከር አገልግሎት ለመስጠት ታቅዶ 6ቱም የተከናወነበትና 4 የማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት በታቀደው መሰረት እቅዱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ ተችሏል፡፡
ከዚህ አንፃር የ2017 የአካዳሚውን እቅድ አፈፃፀም ስንመለከት የተሻለ አፈፃፀም የተመዘገበበት ወቅት መሆኑን ነው ያመላከቱት፡፡ በዘንድሮው 2018 በጀት ዓመትም አካዳሚው እቅድ ሲያዘጋጅ በዋናነት መነሻ ያደረገው የአካዳሚው የ5 ዓመት፣ የ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ እና የ2017 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀምን መነሻ በማድረግ ነው፡፡
እቅዱን ሲያዘጋጅም በየደረጃው ያሉ ስትራቴጂክ አመራሮች እስከ ጠቅላላ ሰራተኞች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ጋር መግባባት ተፈጥሮ ነው ወደ ስራ የተገባው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም በዋናነት አካዳሚው የከተማ አስተዳደሩ የሰጠው ተልዕኮ ስልጠና፣ ጥናትና ምርምር ማማከርና ከማህበረሰብ አገልግሎት ጋር ተያይዞ በመሆኑ የ2018 እቅድም በዓበይት ተግባራት ላይ የሚያተኩር ነው፡፡
ከዚህ አኳያ በያዝነው በጀት ዓመት በከተማ አስተዳደሩ ከወረዳ እስከ ማዕከል ላሉ 6 ሺህ 500 ተሿሚ አመራሮች ስልጠና ለመስጠት የታቀደ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት 1 ሺህ 184 ለሚሆኑት ለመስጠት ታቅዶ 500 ለሚሆኑ ተሿሚ አመራሮች መስጠት ተችሏል፡፡ ይህም የእቅዱን 42 ነጥብ 3 በመቶ መከናወኑን ያመላክታል፡፡
ከስራ አመራር ዳይሬክቶሬት አኳያም በበጀት ዓመቱ 8 ሺህ 500 ለሚሆኑ ከቡድን መሪ እስከ ዳይሬክተር ያሉ ባለሙያዎች በተለያየ ዘርፍ ስልጠና ለመስጠት የታቀደ ሲሆን፣ በዚህ ዘርፍም በሩብ ዓመቱ ወደ 850 ለሚሆኑት ለመስጠት ታቅዶ 623 የሚሆኑት ስልጠናውን ማግኘታቸው ነው የተገለፀው፡፡
ከባለሙያ ጋር ተያይዞም በበጀት ዓመቱ 3 ሺህ 386 ባለሙያ ለማሰልጠን ታቅዷል፡፡ ከዚህ ውስጥ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 338 ባለሙያዎችን ለማሰልጠን የታቀደ ሲሆን፣ ከዚህም 558 የሚሆኑትን በማሰልጠን ከእቅድ በላይ ማከናወን ተችሏል፡፡
አቶ ሽመልስ ለስልጠና ግብዓት የሚሆኑ ነገሮችን ከማቅረብ ጋር ተያይዞም ሰፊ ስራዎች እንደሚሰሩ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ለስልጠና አስፈላጊ የሆኑ ሞጁሎችን ከማዘጋጀት አኳያ በተለይ በያዝነው በጀት ዓመት ለተሿሚ አመራሮች አራት ሞጁሎችን ለማዘጋጀት እቅድ ከመያዙም ሌላ በስራ አመራር ዳይሬክቶሬትም አምስት ሞጁሎችን ለማዘጋጀት መታቀዱን ነው ያመላከቱት።፡
የማሰልጠኛ ሞጁሎች በሚዘጋጁበት ጊዜ መነሻ የሚደረገው በከተማ ደረጃ ያለው የስልጠና ፍላጎት ነው። ለማዘጋጀት የታቀዱት ሞጁሎች መነሻም ከዚህ የሚመነጭ ሲሆን፣ ሁለቱ የስራ ክፍሎችም ከዚህ አንፃር ዝግጅት አድርገው ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከጥናትና ምርምር ጋር ተያይዞ በበጀት ዓመቱ ወደ 15 እንዲሁም በተያዘው ሩብ ዓመት 4 የጥናት እና ምርምር ስራዎችን ለመስራት ታቅዶ፣ ስድስት ማከናወን ተችሏል፡፡ ይህን ለማከናወን ቅድሚያ ፕሮፖዛል ተሰርቶ በሚመለከተው አካል ከፀደቀ በኋላ ወደ ዋናው ጥናት የሚገባ ይሆናል፡፡ በሩብ ዓመቱ የጥናትና ምርምር ውጤት ለማጠናቀቅ በእቅድ ደረጃ ባይያዝም 3 የጥናትና ምርምር ስራዎች ተጠናቅቀው ለግምገማ ዝግጁ ሆነዋል፡፡
እነዚህን የጥናትና ምርምር ስራዎች በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ያሉ በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ለማፀደቅም ኮንፍረንስ እንደሚዘጋጅ ያመላከቱት ዳይሬክተሩ፣ በአንደኛው ሩብ ዓመት 2 ኮንፈረንሶችን ለማዘጋጀት ታቅዶ 3 በማዘጋጀት ከእቅድ በላይ ማከናወን መቻሉን ጠቁመዋል፡፡ ከማማከርና ከማህበረሰብ አገልግሎት ጋር ተያይዞ የሚሰጡ ስልጠናዎችም ተቋማት ላይ ትኩረት የሚደረግ ነው፡፡ ለአብነትም ተቋማት ምን አይነት የማማከር አገልግሎት ይፈልጋሉ? የሚለውን መሰረት አድርጎ የሚኬድበት ይሆናል፡፡
ይህንንም በተመለከተ ለተቋማት ደብዳቤ ቢፃፍም በወቅቱ ምላሽ የሚሰጡ ብዙ አይደሉም፡፡ ሆኖም ግን በበጀት ዓመቱ 7 የማማከር አገልግሎት ለመስጠት እቅድ ተይዞ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 2 የማማከር ፕሮጀክት ፕሮፖዛል ለማዘጋጀት ታቅዶ ፍላጎቱ በወቅቱ መምጣት ባለመቻሉ ማከናወን አልተቻለም፡፡
አካዳሚው ይህን ችግር ለመፍታት ከዚህ በፊት ያደረጋቸውን የጥናትና ምርምር ስራዎችን መነሻ በማድረግ የጥናትና ምርምሩ ምክረ ሃሳብ ምንድን ነው? የሚለውን ታሳቢ አድርጎ የማማከር አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ ከማህበረሰብ አገልግሎት ጋር ተያይዞም ማህበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት ማህበረሰቡ ጋር ድረስ በመሄድ እየተሰራ ነው፡፡ ለአብነትም በ2017 በጀት ዓመት ‘ለነገዋ’ የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል፣ የአዲስ አበባ አረጋዊያን ማህበር እንዲሁም ተማሪዎች ጋር ተያይዞ ብዙ የማህበረሰብ አገልግሎቶች ተሰርተዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የዝግጅት ምዕራፍን የተግባር ምዕራፍ መሆን አለበት ባለው መሰረት ሳምንቱን ሙሉ ቀንና ሌሊት (7/24) ስራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ እንደ አካዳሚው ከዚህ በፊት ባልነበረ የዝግጅት ምዕራፉ ወደ ተግባር የተገባበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው፣ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከተያዘው እቅድ አኳያ ችግሮች ቢኖሩም አፈፃፀሙ የተሻለ መሆኑ የተገመገመበት ነው፡፡
በግምገማው በመሰረታዊነት ከተለዩ ችግሮችም ዋነኛው የሰው ኃይል ችግር ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የኢንስቲትዩቱ መዋቅር የሚፈቅደው የሰው ኃይል 325 ሲሆን፣ መያዝ አለበት የሚባለው ደግሞ 250 ነው፡፡ አካዳሚው በእነዚህ መደቦች ላይ እስከ አሁን ያለው የሰው ኃይል ቁጥር ግን 124 ብቻ ነው፡፡ ይህም ካለው አጠቃላይ የሰው ኃይል ድርሻ 34 ነጥብ 5 በመቶ ብቻ መሟላቱን ያሳያል፡፡
በተለይ ዓላማ አስፈፃሚ በሚባሉት ስልጠና፣ ምርምር፣ ማማከርና ማህበረሰብ አገልግሎት የስራ ክፍሎች ጋር ተያይዞ ባለሙያ የሆኑ ሰዎችን ይፈልጋል ከዚህ አኳያ ያሉ ክፍተቶችን ለመሸፈን አካዳሚው ከፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ጋር በመነጋገር ባለሙያዎችን የማሟላት ስራ እየሰራ በመሆኑ ከ22 በመቶ ወደ 34 በመቶ ማደግ ችሏል፡፡
በተጨማሪም ተቋሙ ተባባሪ አካላትን በማስታወቂያ በመጋበዝ ስራዎችን እየሰራ እንደሆነ አመልክተው በዚህም በተለይ የአሰልጣኞች ተባባሪ አካላትን እና የምርምር ተባባሪ አካላትን የመመልመል ስራዎችን እንደሚሰራ ተናግረዋል። ቅንጅታዊ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ችግሮችን የመፍታት አካሄድም ሌላው አሰራር ሲሆን ከዚህም ጋር ተያይዞ በቡድን የመስራት ባህል እየጎለበተ መጥቷል፡፡
ሌላው እንደተቋም የተለየው መሰረታዊ ችግር ተቋሙ የሚገኘው ለአስፓልት ቅርብ በሆነ የኪራይ ህንፃ ላይ እንደመሆኑ ከፍተኛ የሆነ የማሰልጠኛ ቦታ እጦት አለበት፡፡ የማሰልጠኛ ክፍሎች ማነስና መጥበብ ብቻ ሳይሆን መንገድ ዳር በመሆኑ የድምፅ ብክለት ያሉት አምስት የማሰልጠኛ ክፍሎችም የድምፅ መከላከያ ስላልተገጠመላቸው ከአንዱ ማሰልጠኛ ክፍል የሚወጣው ድምፅ ሌላውን የሚረብሽ መሆኑ በራሱ ችግር የሚፈጥር ነው፡፡
ተቋሙ ጎሮ አካባቢ የራሱን ህንፃ እያስገነባ መሆኑ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል፡፡ የህንፃው ግንባታ እስኪጠናቀቅም ችግሩን ለመፍታት ከሌሎች ተቋማት ጋር ትስስር ተፈጥሯል። በበጀት ዓመቱ 10 ተቋማት የተለዩ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ከዘጠኙ ጋር አካዳሚው ተፈራርሞ ወደ ስራ ገብቷል። ከእነዚህም የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢኒስቲትዩት እንዲሁም የአፍሪካ ልህቀት ማዕከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በሸዋርካብሽ ቦጋለ