የኮከብነት ዘውዱን ማን ያጠልቀው ይሆን?

You are currently viewing የኮከብነት ዘውዱን ማን ያጠልቀው ይሆን?

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) የ2025 ለአህጉሪቱ ኮከብ እግር ኳስ ተጫዋች ዘውድ ለማጥለቅ እ.ኤ.ኤ ህዳር 19 ቀን 2025 በሞሮኮ ቀጠሮ ይዟል፡፡ ካፍ ለ2025  የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማት የተመረጡትን የመጨረሻ አስር ዕጩዎች ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ የኮከቦች ስብስብ ባለፈው የውድድር ዘመን በአፍሪካም ሆነ በአውሮፓ ሜዳዎች ድንቅ ብቃትን ያሳዩ ተጫዋቾችን ያካተተ ሲሆን፣ ለአሸናፊነትም ትልቅ ሽሚያ እንደሚኖር ተጠብቋል።

ከእነዚህ ኮከቦች መካከል በሊቨርፑል እግር ኳስ ክለብና የግብፁ ኮከብ ሙሀመድ ሳላህ (በ2017 እና በ2018  አሸናፊው)፣ በፒኤስጂ የውድድር ዘመኑን በአራት ዋንጫዎች ያጠናቀቀውንና የሞሮኮውን ኮከብ አሽራፍ ሀኪሚ፣ እንዲሁም በቅርቡ ወደ ጋላታሳራይ የተዘዋወረውን የናይጄሪያ አጥቂ ቪክቶር ኦስሚህንን እና በቶተንሀም ሆትስፐር መሃል ሜዳውን የተቆጣጠረውን ፔፕ ማታሳርን ይገኙበታል። የባለፈው ዓመት አሸናፊ አድሞላ ሉክማን በዕጩዎቹ ውስጥ መካተት ያልቻለ ሲሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት 2ኛ ሆኖ የጨረሰው ሞሮኮአዊው የፒኤስጂ ተጫዋች አችራፍ ሀኪሚ በዚህ ዓመት ትልቅ ግምት ስለማግኘቱ አፍሮ ስፖርት ዘግቧል፡፡

ከአስሩ ዕጩዎች መካከል ስምንቱ የሚጫወቱት በአውሮፓ ከፍተኛ ሊጎች ውስጥ ሲሆን፣ ሁለቱ ኮከቦች (ፊስቶን ማየሌ እና ኡሳማላምሊዊ) በአፍሪካ ውስጥ ባሉ ክለቦች መካከል በሚካሄድ የካፍ ውድድሮች ባሳዩት አስደናቂ ብቃት ዕጩ መሆን ችለዋል። ይህ የአፍሪካ የውስጥ ሊጎችም ዓለም አቀፍ ደረጃ ላይ ያሉ ኮከቦችን ማፍራት መቻላቸውን ያሳያል። እንደዚሁም እነዚህ ተጫዋቾች በዋናነት ዕጩ መሆን የቻሉት በካፍ ሻምፒየንስ ሊግ እና ካፍ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ባሳዩት አስደናቂ ብቃት ነው።

ይህ ደግሞ የካፍ ኢንተር ክለብ ውድድሮች ደረጃ ከፍ ማለቱን ያሳያል። እነዚህ ውድድሮች የአፍሪካ ተጫዋቾች ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኙ የሚያስችል ጠንካራ መድረክ መሆናቸውንም እንደሚያረጋግጥ ናይጄሪያዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ፒተርስ ኦኮቻ ይገልጻል።

በሌላም በኩል በአፍሪካ ውስጥ ያሉ ክለቦች ተጫዋቾች ዋጋ እና ብቃት ከአውሮፓ ተጫዋቾች ጋር እኩል ተፎካካሪ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ይህም የአውሮፓ ክለቦች በአፍሪካ የውስጥ ሊጎች ላይ ያላቸውን ክትትል እንዲያጠናክሩ ያደርጋል ተብሏል።

የ2025 የአፍሪካ ኮከብነት ሽልማት ዋነኛ ፍልሚያ በተለይም በሙሀመድ ሳላህ እና ችራፍ ሀኪሚ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ሳላህ በሊቨርፑል ላለፉት በርካታ ዓመታት ያሳየው የማያቋርጥ ድንቅ ብቃት፣ ግቦችን የማስቆጠርና የማቀበል ችሎታው ለዚህ ሽልማት ዋነኛው መመዘኛ ሆኖ ቀርቧል።

በዕጩዎቹ ዝርዝር ውስጥ ብቸኛ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች የሆነው ሞሮኳዊው ሀኪሚ በበኩሉ በውድድር ዘመኑ ከፒኤስጂ ጋር አራት የሀገር ውስጥ ዋንጫዎችን (የዩኤኤፍኤ ቻምፒየንስ ሊግን ጨምሮ) ማንሳቱ፣ እንዲሁም በሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ወሳኝ ሚና መጫወቱ ትልቁ ጥንካሬው ነው። ሀኪሚ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተከታታይ 2ኛ በመሆን ሽልማቱን በቅርብ ርቀት ማጣቱ፣ ዘንድሮም ለዋንጫ ከፍተኛ ግምት እንዲያገኝ አድርጎታል።

በቱርኪዬ ለጋላታሳራይ እግር ኳስ ክለብ እየተጫወተ የሚገኘው ናይጄሪያዊው ቪክቶር ኦስሚህን ሌላኛው ዕጩ ተጨዋች ሲሆን፣ 2023 አሸናፊ የሆነው ኦስሚህን በጣሊያኑ ናፖሊ ያሳየው የግብ ማስቆጠር ችሎታ እና በናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ያለው ትልቅ ሚና ዕጩ እንዲሆን አስችሎታል። ምንም እንኳን የ2024 የሽልማቱ አሸናፊ አድሞላሉክማን (ከናይጄሪያ) በዕጩነት ባይካተትም፣ ኦስሚህን የሀገሩን ክብር ለማስጠበቅ ወደፍጻሜው ተመልሷል። ወጣቱ ሴኔጋላዊው ፔፕማታሳር በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በቶተንሀም ሆትስፐር መሃል ሜዳ ወሳኝ ሚና በመውሰድ ባሳየው የማያቋርጥ የብቃት እድገት ዕጩ ሆኗል። የእሱ ጨዋታዎች በጠንካራው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መሃል ሜዳ ያለውን የቴክኒክ ብቃትና ጥንካሬ የሚያንፀባርቁ ናቸው። ከሌላው ሴኔጋላዊ ኮከብ ኢሊማን ንዲያዬ ጋር ሆነው የአዲሱን የሴኔጋል ወጣት ትውልድ ስኬት ይወክላሉ።

የጊኒው ኮከብ ሰር ሁጊራሲበ ጀርመን ቡንደስሊጋ የውድድር ዘመን መጀመሪያ ላይ ባሳየው አስደናቂ የግብ ማሽን ብቃት በአውሮፓ ትኩረት ስቧል። የሱ ፈጣን የግብ ብዛት ሪከርዶችን ሰብሯል፤ ይህም በካፍ ምርጫ ኮሚቴ ዘንድ ከፍተኛ ግምት እንዲያገኝ አስችሎታል። የተጫዋቹ ዕጩነት በአውሮፓ መካከለኛ ክለቦች ውስጥም ቢሆን የላቀ ብቃት ማሳየት ለሽልማት ዕጩነት መብቃት እንደሚቻል ያሳያል።

የ2025 የካፍ የአፍሪካ ምርጥ ተጫዋች ሽልማት በሙሀመድ ሳላህ፣ አችራፍ ሀኪሚ እና ቪክቶር ኦስሚህን መካከል የጦፈ ፉክክር እንደሚካሄድ ይጠበቃል። ይሁን እንጂ እንደ ፔፕ ማታሳር እና ሰር ሁጊራሲ ያሉት አዲስ ኮከቦች ያልተጠበቀ ውጤት ይዘው ሊመጡ ይችላሉ።

የ2024 የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች አሸናፊ የነበረው ናይጄሪያዊው አድሞላ ሉክማን በዕጩዎቹ ዝርዝር ውስጥ አለመካተቱ አግራሞትን የፈጠረ ሲሆን ምንም እንኳን በክለቡ አታላንታ የላቀ የውድድር ዘመን ቢኖረውም፣ የካፍ ኮሚቴ በሌሎች ተጫዋቾች ላይ ትኩረት አድርጓል። ይህ ደግሞ በሽልማቱ ላይ ያለው ፉክክር ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ ያመላክታል ሲሉ የካፍ ድምጽ ሰጪ ኮሚቴ አባላት ይገልጻሉ።

ካፍ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ዘርፎች የላቀ ብቃትን ያሳዩ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ይሸልማል። የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝ አንዱ ሲሆን የ2025 የአሰልጣኝ ሽልማት ትልቅ ግምት ከተሰጣቸው ዕጩዎች መካከል የኬፕ ቨርዴን ብሔራዊ ቡድን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዓለም ዋንጫ እንድታልፍ ያደረጉት አሰልጣኝ ቡቢስታ ይገኙበታል። የቡቢስታ ስኬት በትንሽ ሀገር ውስጥ ትልቅ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል የሚያሳይ አብነት ነው። ናይጄሪያዊው ያኑ ኢስተር ኦኮሮንኮው እና ራሽዳት አጄባዴ በሴት ተጫዋቾች ዘርፍ በዕጩነት የቀረቡ ሆነዋል፡፡

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ካፍ የራሱን “የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች” ሽልማት መስጠት የጀመረው በ1992 ሲሆን የመጀመሪያው አሸናፊ ተጨዋችም ጋናዊው የቀድሞ ኮከብ እግር ኳስ ተጫዋች አቤዲ ፔሌ ስለመሆኑ የካፍ መረጃ ያሳያል፡፡ ካፍ የሽልማት ስነ ስርዓቱን ማካሄድ ከመጀመሩ አስቀድሞ ሽልማቱ በፈረንሳይ እግር ኳስ መጽሔት (France Football Magazine) አማካኝነት ከ1970 አንስቶ ይሰጥ ነበር።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) “የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች” ሽልማትን አራት ጊዜ በማሸነፍ ካሜሮናዊው ሳሙኤል ኤቶ እና የአይቮሪ ኮስቱ ያያ ቱሬ ክብረ ወሰኑን ይጋራሉ። ዲዲዬ ድሮግባ፣ ኤልሃጂ ዲዩፍ፣ ንዋን ኮካኑ፣ ሙሀመድ ሳላህ፣ ሳዲዮ ማኔ ያሉ ተጫዋቾች ደግሞ ሁለት ሁለት ጊዜ ያሸነፉ አፍሪካውያን ከዋክብት ናቸው ይላል ካፍ ኦንላይን ድረ- ገጽ መረጃ፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review