የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በመዲናዋ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።
የጉብኝቱ ተሳታፊ የሆኑት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ ሎሚ በዶ እንደገለጹት፣ የአዲስ አበባ ከተማ እጅግ በጣም በአጠረና በፈጠነ ሁኔታ እየተለወጣች ያለች ከተማ መሆኗን ተመልክተናል ብለዋል፡፡
ባለፉት ቀናት “በመደመር እይታ የዘርፎች እምርታ” በሚል ርዕሰ ጉዳይ የተለያዩ ሴክተሮችን ለማየት ጥረት አድርገናል ያሉት ምክትል አፈ ጉባኤዋ፣ ምናባዊ ከሆነው እሳቤ በመነሳት ለመስራት ያስቀመጥናቸወን ግቦች ምን ያክል አሳክተናል የሚለውን በተጨባጭ መሬት ላይ ያለው ለመመልከት ነው ጉብኝት እያደረግን ያለነው ብለዋል፡፡
ይህም የስልጠናው አንዱ አካል መሆኑን የጠቁሙት ምክትል አፈ ጉባኤዋ፣ በትናንትናው እለት በኦሮሚያ ክልል በግብርናው ዘርፍ የተሰሩ የልማት ሰራዎችን መመልከታቸውንም አክለዋል፡፡
በክልሉ የገጠሩን ልማት ያፋጠኑና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ያደረጉ ከፍተኛ ስራዎች መሰራታቸውንም ተመልክተናል ነው ያሉት ምክትል አፈ ጉባኤዋ፡፡
ምክትል አፈ ጉባኤዋ አክለውም፣ በቢሸፍቱ ከተማ እየተከናወነ ያለውን ልማት መመልከታቸውን ገልጸው፣ በዚህም የከተማውን ነዋሪ ተጠቃሚ ለማድረግና ከተማውን የቱሪስት መስህብ እንዲሆን የሚያስችሉ አኩሪ ስራዎች ተሰርተው በውጤት መጠናቀቃቸውን ተመልክተናል ብለዋል፡፤
ሌላኛው የጉብኝታቸው አካል የአዲስ አበባ ከተማ መሆኗን የገለጹት ወይዘሮ ሎሚ፣ አዲስ አበባን ያገኘንበት ደረጃ እጅግ በጣም ከፍ ባለ እና በሚያኮራ ደረጃ ነው ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ የኮንፈረንስ እና የየንግድ ማዕከል እንዲሁም አካታች ከተማ እንድትሆን የተሰራው ስራ እጅግ በጣም የሚያኮራ ነው ብለዋል፡፡
በከተማዋ ውስጥ የሚገኙት ከ76 በላይ የሚሆኑት ወንዞች ከዚህ ቀደም የቆሻሻ መውረጃ እንደነበሩ የገለጹት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይሰሮ ሎሚ፣ በቁርጠኝነት በተሰራው የወንዞች ዳርቻ የልማት ስራ በአሁኑ ጊዜ ወንዞቹ ንጹህ፣ ማራኪና ሳቢ፣ የሰው ልጅ ንጹህ አየር የሚያገኝባቸው መሆን እንደቻሉ ተመልክተናል ነው ያሉት፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ በከተማዋ ውስጥ የተገነቡ የንግድ ማዕከላት፣ የሰንበት የገበያ ቦታዎች እና በመዲናዋ የሚስተዋውን የቤት እጥረት ለመፍታት የተሰራው ስራ ለሌሎች ከተሞችም ምሳሌ የሚሆን ስራ መሆኑን ተመልክተናል ነው ያሉት ምክትል አፈ ጉባኤዋ፡፡
በአስማረ መኮንን