እንደ ሀገር በአጭር ጊዜ ከተሰሩ ስራዎች የተማርነው ይቻላልን ነው ሲሉ የሶማሌ ክልል ርዕለ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ገለፁ።
ከማለዳው ጀምሮ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በአዲስ አበባ ከተማ የተሰሩ የተለያዩ የልማት ስራዎች ጉብኝት አድርገዋል፡፡
በጉብኝቱ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ፣ በአዲስ አበባ ቱሪዝምን መሰረት ያደረጉ የልማት ስራዎች መጎብኘታቸውን ተናግረዋል።
በከተማዋ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ማሳየቷን የገለፁት ርዕሰ መስተዳደሩ፣ ይህ መሆኑ የብልፅግና ፓርቲ አዲስ እሳቤ ይዞ ከመስራቱም ባሻገር፣ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት የመጨረስ ባህል መዳበሩን እንደሚያሳይም አመላክተዋል።

እንደ ሀገር በአጭር ጊዜ ከተሰሩ ስራዎች የተማርነው ይቻላልን ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፣ በዚህ ፍጥነት የታየው ኢትዮጰያ እምቅ ሀብት እና አቅም እንዳላት ነው ብለዋል።
በተለይም ለተመዘገበው ልማት መፍጠር እና የመፍጠን እሳቤ በፓርቲው መተግበሩ በከተማዋ የተመዘገቡት ስኬቶች ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።
በአሁኑ ጊዜ ካልፈጠርን እና ካልፈጠንን ያደጉ ሀገሮች የደረሱበት ደረጃ መድረስ እንደማይቻል በመግለፅ፣ ከዚህ ቀደም ፕሮጀክቶች በሚሰሩበት ፍጥነት ሀገር ለመለወጥ እሳቤን መቀየር ማስፈለጉን አመላክተዋል።
የአዲስ አበባ መለወጥ የሚያሳየው፣ የብልፅግና ፓርቲ በአዲስ እሳቤ ኢትዮጰያን ምን ያህል እየለወጠ መሆኑንም ነው ብለዋል።
በዛሬው እለት በመዲናዋ የጎበኘነው የልማት ስራ በእጅጉ የሚያኮራ ነው ያሉት አቶ ሙስጠፌ፣ በሶማሌ ክልል የኮሪደር ልማት ሲሰራ ከአዲስ አበባ ብዙ ልምድ እና ተሞክሮ መወሰዱን ጠቀሰዋል።
በሔለን ተስፋዬ