የህብረተሰቡን የኑሮና የገቢ አቅም ያገናዘበ የንግድ ስርዓት እንዲፈጠር መንግስትና ህዝቡ በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ።
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በንግድ እና በህብረት ስራ ማህበራት ጽህፈት ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያተኮረ ከህዝብ ጋር የውውይት ባካሄደበት ወቅት የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ተስፋዬ እንደ ገለጹት የህብረተሰቡን የኑሮ አቅም ያገናዘበ የንግድ ስርዓት እንዲፈጠር መንግስትና ህዝቡ በጋራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡
የንግዱ ማህበረሰብ ህብረተሰቡን በትክክል ማስተናገድ የፊት ለፊት ውይይት በጣም ጠቃሚ መሆኑን ያመላከቱት ስራ አስፈጻሚው የመንግስት ተቋማት ስኬታማ ስራ እንዲሰሩና የህዝብ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ህዝቡም ለአስፈጻሚ አካላቱ ጠንካራ ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

በመድረኩ ተሳታፊዎች ከሸቀጣሸቀጥ አቅርቦት እና ዋጋ ጋር በተያያዘ በርካታ ሀሳብ፤ አስተያየት እና ጥያቄዎች ያነሱ ሲሆን የክፍለ ከተማው የስራ ሃላዎች ምላሽ እና ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ዘይነባ ጠሃ በበኩላቸው የእንጠያየቅ መድረኩ ዓላማ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው የልማት ስራዎችን ለህዝቡ ተገራሽ ማድረግ፣ በፍትሃዊ መንገድ እንዲጠቀም ማስቻልና ችግሮችም ካሉ ፊት ለፊት ለመወያየት ነው ብለዋል።
በመድረኩ የህብረተሰቡን የኑሮ አቅም ያገናዘበ የንግድ ስርዓት እንዲፈጠር መንግስትና ህዝቡ በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን ህገወጥ ነጋዴዎች የሚፈጥሩትን አሻጥር ለመከላከል ህብረተሰቡ ከመንግስት መዋቅሩ ጋር በትብብር ሊሠራ ይገባል የሚል መልዕክትም ተላልፏል።
በምትኩ ተሾመ