ማንችስተር ሲቲ ከሊቨርፑል ፦ አርሰናልን ለመከተል የሚደረገው ሩጫ

You are currently viewing ማንችስተር ሲቲ ከሊቨርፑል ፦ አርሰናልን ለመከተል የሚደረገው ሩጫ

AMN-ጥቅምት 30/2018 ዓ.ም

በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት መርሃግብር እጅግ ተጠባቂው ጨዋታ ዛሬ ይደረጋል።

ማንችስተር ሲቲ በሜዳው ኢትሃድ ሊቨርፑልን የሚያስተናግድበት ፍልሚያ አርሰናልን ለመገዳደር የበለጠ አቅም ያለው ክለብ የሚታይበት ሊሆን ይችላል።

ትናንት ምሽት አርሰናል በሰንደርላንድ ነጥብ መጣሉን ተከትሎ ሁለቱም ክለቦች ሦስት ነጥቡን ለማግኘት መቋመጣቸው አይቀርም።

ማንችስተር ሲቲ በመሀል በአስቶንቪላ ቢሸነፍም ሰሞነኛ ብቃቱ ጥሩ የሚባል ነው።

የፔፕ ጋርዲዮላው ቡድን በፕሪሚየር ሊጉ ድንቅ ጉዞ ላይ የነበረው ቦርንማውዝን ፣ በቻምፒየንስ ሊጉ ደግሞ ቦሩሲያ ዶርትመንድን በማሸነፍ ነው ለዛሬው ጨዋታ የሚቀርበው።

ሊቨርፑልም ከተከታታይ ሽንፈት በኋላ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አስቶንቪላ እና ሪያል ማድሪድን በመርታት አገግሟል።

ሁለቱ ክለቦች በተለይ የርገን ክሎፕ ቀዮቹን ከተረከቡ እና ፔፕ ጋርዲዮላም የእንግሊዝን ምድር ከረገጠ በኋላ ለዓመታት ከፍ ያለ ደረጃ የሚሰጠው ፉክክር አሳይተዋል።

ምንም እንኳን የማንችስተር ሲቲ የበላይነት ቢበዛም የሊጉን ዋንጫም ተፈራርቀውበታል።

ያለፉትን ስምንት የውድድር ዓመታት የሊግ ዋንጫዎች ጉዞአቸው ኢትሃድ አልያም አንፊልድ ነበር።

ዘንድሮ አርሰናል ይህን ድግግሞሽ ለመስበር የተዘጋጀ ይመስላል።

ሁለቱም ቡድኖች መድፈኞቹን የመፎካከር አቅም አላቸው።

ይህን ለማሳየት ትልቅ ጨዋታ ማሸነፍ ይኖርባቸዋል። በዚህ ምክንያት የዛሬው ጨዋታ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ትልቅ ትርጉም አለው።

ማንም ሳይጠብቃቸው ሊቨርፑልን ለ20ኛ የሊግ ድል ያበቁት አርነ ስሎት ባለፈው ዓመት ሲቲን ሁለት ጊዜ ገጥመው የበላይነታቸውን አሳይተዋል።

ሁለቱንም የሊግ ጨዋታዎች በተመሳሳይ 2ለ0 ማሸነፍ የቻሉት ኔዘርላንዳዊው አሰልጣኝ ዘንድሮ ቡድናቸው ከሜዳው ውጪ ተቸግሯል።

የመርሲሳይዱ ክለብ ከሜዳው ውጪ ካደረጋቸው ሦስት የመጨረሻ ጨዋታዎች በክሪስታል ፓላስ ፣ በቼልሲ እና በብሬንትፎርድ ተሸንፏል።

በሲቲ በኩል ኧርሊንግ ሃላንድ ዛሬ ሁለት ግብ ካስቆጠረ ታሪክ ይሰራል። በ107 ጨዋታዎች 98 የፕሪምየር ሊግ ግብ ያስቆጠረው አጥቂ ዛሬ 100 ከደረሰ በጥቂት ጨዋታዎች እዚህ ቁጥር ላይ የደረሰ ቀዳሚው ተጫዋች ይሆናል።

እንግሊዛዊው የቀድሞ አጥቂ አለን ሺረር በ124 ጨዋታ 100 ግቦችን በማስቆጠር ክብረወሰኑን ማያዝ ችሏል።

ስፔናዊው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ 1000ኛ ጨዋታውን ዛሬ ይመራል።

ስልጠናን በባርሰሎ የጀመረው ፔፕ ባየርን ሙኒክ እና ማንችስተር ሲቲን በ999 ጊዜ መርቷል። ከእነዚህ ውስጥ በ715ቱ ጨዋታዎች ባለድል ሆኗል።

ምሽት 1:30 በኢትሃድ የሚደረገው የዛሬ ጨዋታ በዋና ዳኛው ክሪስ ካቫናህ ይመራል።

በሌሎች የዛሬ ጨዋታዎች በተመሳሳይ 11 ሰዓት አስቶንቪላ ከቦርንማውዝ ፣ ብሬንትፎርድ ከኒውካስትል ፣ ክሪስታል ፓላስ ከብራይተን እንዲሁም ኖቲንግሃም ፎረስት ከሊድስ ዩናይትድ ይጫወታሉ።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review