ኤሌክትሪክ እንዳይቋረጥና ሲቋረጥም ፈጣን መረጃ በመስጠት የሃይል ተደራሽነትን ማስፋት የሚያስችል “ስካዳ” የተሰኘ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመተግበር እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ፡፡
የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አንዋር አብራር እንዳሉት፤ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት የዜጎችን የኑሮ ደረጃ በማሻሻልና የኢንዱስትሪ ልማትን በማስፋፋት ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ ነው፡፡
የለውጡ መንግስት አዳዲስ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማትንና ብዝኃ የሀይል ማመንጫዎችን በማስፋፋትና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ፍትሐዊ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
ያረጁ የኤሌክትሪክ መስመሮችን መልሶ በመገንባት እንዲሁም በአዲስ በመተካት የትራንስፎርመሮችን አቅም በማሳደግ የኤሌክትሪክ ተደራሽነቱን ከዚህ በላይ ለማሳደግ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ የአራት ሺህ ትራንስፎርመሮችን አቅም ማሳደግና ከ625 ኪሎ ሜትር በላይ ያረጁ መስመሮችንና ፖሎችን በአዲስ መቀየራቸውን ጠቅሰው፤ በክልሎችም ተመሳሳይ ሥራ በማከናወን የሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽፋን 54 በመቶ ማድረስ እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡
በ2018 በጀት ዓመትም ለ800ሺህ ደንበኞች ቆጣሪ ለማሰራጨት እቅድ መያዙንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡
አገልግሎቱ የዜጎችን ፍትሐዊ የሀይል ተደራሽነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ጭምር እየተጠቀመ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በዚህም አገልግሎቱ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ማሳደግ የሚያስችል ዘመኑን የዋጀ “ስካዳ” የተሰኘ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ለመማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
“ስካዳ” በየትኛውም ቦታ የኤሌክትሪክ ሃይል ሲቋረጥና ከመቋረጡ በፊት ቢሮ ውስጥ ሆኖ መቆጣጠር የሚያስችል ቴክኖሎጂ መሆኑን ገልጸው፤ የትኛው መስመር የትኛው ቦታ ላይ እንደተበላሸ ለማወቅ ያግዛል ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።
ቴክኖሎጂው የኤሌክትሪክ ሃይል እንዳይቆራረጥ ቀድሞ መረጃ በመስጠት ደንበኞች ከመደወላቸው በፊት ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደሚያስችልም ገልጸዋል፡፡