የአመራሩ ቁርጠኝነት፣ በፈጠራ፣ በፍጥነትና በጥራት መስራት ለሁለንተናዊ ብልፅግና መረጋገጥ አስፈላጊ ነው ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዝዳንትና የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለፁ።
“በመደመር መንግሥት እይታ፣ የዘርፎች እምርታ” በሚል መሪ ሀሳብ ከፌደራል፣ ከክልል፣ ከዞን እንዲሁም ከከተማ አስተዳደሮች ለተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለተከታታይ 11 ቀናት ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቋል።
የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዝዳንትና የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በመደመር መንግሥት ላይ የማጠቃለያ ስልጠና ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በማጠቃለያ ስልጠና ላይ እንደገለፁት የአመራሩ ቁርጠኝነት፣ በፈጠራ፣ በፍጥነትና በጥራት መስራት ለሁለንተናዊ ብልፅግና መረጋገጥ አስፈላጊ ነው።

በስልጠናው የመደመር መንግሥት ፅንሰ ሀሳብ፣ መንገድና መዳረሻ ግቦቹ የተዳሰሱ ሲሆን በዚህም በመደመር መንግሥት መርህ የሚመራው ፓርቲው አመራሮች በፈጠራ፣ በፍጥነትና በብዛት ስራዎችን በማከናወን የህዝባችን ሁለንተናዊ ጥያቄ ከመመለስ በላይ የሀገራችን ራዕይ ለማሳካትና ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ በሚረዳ መንገድ መምራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትኩረት የሚሹ ግቦችን በየፈርጁ በመለየት አቅጣጫ ያስቀመጡ ሲሆን ፋይዳ፣ 5 ሚሊዮን ኮደሮች፣ የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ስራዎች፣ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች፣ የምርጫ ምቹነትና የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም አጀንዳዎች በ100 ፐርሰንት ለማሳካት መትጋት የሚገባን ግቦች ናቸው ሲሉም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በማጠቃለያ ገለጻ እንዳብራሩት መደመር ትውልድን ወደ ብልፅግና የሚያደርስ መንገድ ነው።
የመደመር መንግሥት ለሀገር ብልፅግና ባለአደራ መሆኑን ተናግረው በፈጠራና በፍጥነት ጥራትና ብዛትን እውን ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለው እንዳብራሩት በብዝሀ ዘርፍ ትስስር ወደ ስልጣኔ ሽግግር ማምጣት ይገባል።
የሀሳብ ሉዐላዊነት የብልፅግና መሰረት እንደሆነ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሁሉም የፓርቲው አመራር በዚህ አግባብ በመትጋት ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ አለበት ብለዋል።
የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ባለፉት 11 ቀናት በስልጠና በውይይትና በመስክ ጉብኝትና በማጠቃለያው ገለጻ ያገኟቸውን እውቀትና ልምዶች በዕቅድ በማካተትና ወደ ስራ በመቀየር የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ለማድረግ በሚደረግ ጥረት ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።