በኅብረተሰብ ተሳትፎ ምቹ የመኖሪያ አካባቢን የመፍጠር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ገለፀ፡፡
ኮሚሽኑ የ2018 ዓ.ም የኅብረተሰብ ተሳትፎ የአካባቢ መሰረተ ልማት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 በብሩህ ተስፋ የጋራ መኖሪያ ቤት አካሄዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ ፀሐይ ኪባሞ በከተማችን ያለው ኅብረተሰብ ሀብቱን ፣ ጉልበቱን ፣ እውቀቱን እና ገንዘቡን ሳይሳሳ ባደረገው ተሳትፎ በከተማዋ አስደማሚ ለውጥ መጥቷል ብለዋል።
አሁንም ከማኅበረሰቡ ጋር በቅንጅት እና በትብብር በመስራት የብሩህ ተስፋ የጋራ መኖሪያ ቤትን ጨምሮ በ2018 በጀት ዓ.ም 200 ብሎኮችን ሞዴል በማድረግ በከተማዋ ምቹ የመኖሪያ አካባቢ ለመፈጠር እየተሰራ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሯ ገልጸዋል።
በኅብረተሰብ ተሳትፎ ለነዋሪዎች ምቹ የመኖሪያ አካባቢ የመፍጠር ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉም ብለዋል።
ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ 65 በመቶ የማኅበረሰቡን የተሳትፎ አቅም በመጠቀም እና 35 በመቶ የመንግስትን ድጎማ በማካተት እንደሚሰራ ምክትል ኮሚሽነሯ ገልጸዋል ።
በኮሚሽኑ የሚሰሩት እና የሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፎን የሚጠይቁትን በማካተት በከተማችን ካለው የፕሮጀክት አፈጻጸም አንጻር፣ ፕሮጀክቱ በ3 ወር ጊዜው ውስጥ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡
በዳንኤል መላኩ