በተቀናጀ መንገድ ሕገ-ወጥ የውጭ ምንዛሪ አሻጥሮችን ሲፈጽሙ የተደረሰባቸው አንድ መቶ አስራ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

You are currently viewing በተቀናጀ መንገድ ሕገ-ወጥ የውጭ ምንዛሪ አሻጥሮችን ሲፈጽሙ የተደረሰባቸው አንድ መቶ አስራ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

AMN ህዳር 1/2018

በተቀናጀ መንገድ ሕገ-ወጥ የውጭ ምንዛሪ አሻጥሮችን ሲፈጽሙ የተደረሰባቸው አንድ መቶ አስራ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎቱ ለኤኤምኤን በላከው መረጃ እንዳስታወቀው፥ መንግሥት ተግባራዊ ያደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በመጻረር በተደራጀ መንገድ በሚፈጽሙ ሕገ-ወጥ የውጭ ምንዛሪ አሻጥሮች ዙሪያ በተቀናጀ መልኩ ምስጢራዊ የመረጃ ስምሪት ሲከናወን ቆይቷል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የክልል የፀጥታ አካላት እና በህብረተሰቡ ጥቆማ በተደረገ የተቀናጀ ሥምሪት በፋይናንስ አሻጥር የተሰማሩ አንድ መቶ አስራ ሁለት ኢትዮጵያውያንና የተለያዩ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን፤ ከሕገ -ወጥ ተግባሩ ጋር ትስስር የነበራቸው አምስት መቶ አስራ ዘጠኝ የባንክ አካውንቶች መታገዳቸውን እንዲሁም የተለያዩ ኤግዚቢቶች መያዛቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡

ሕገ- ወጥ ሃዋላዎች ፣ የገንዘብ ዝውውሮች፣ የውጭ ምንዛሪ ስወራዎች ፣ የግብር ስወራዎች፣ ሕገ- ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ የማስመሰልና ሌሎች ተመሳሳይ ወንጀሎች በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያስከትሉ እንዲሁም አሸባሪዎችንና የታጠቁ ቡድኖችን ለመደገፍ ሲውሉ መቆየታቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡

በተለይም ሕገ- ወጥ በሆኑ ዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች፤ ሕገ- ወጥ የውጭ ምንዛሪ ማስተላለፊያ መተግበሪያዎች፤ የክሪፕቶ ከረንሲ መተግበሪያዎች፤ ሕገ-ወጥ የሃዋላ አዘዋዋሪዎችና ደላላዎች፤ በወጪና ገቢ ንግድ ላይ አሻጥር የፈፀሙ አስመጪዎችና ላኪዎች እንዲሁም ሕጋዊ ንግድ ሳይኖራቸው በሕገ-ወጥ ሃዋላ ላይ በመሰማራት ከፍተኛ ገንዘብ በማንቀሳቀስ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ባደረሱ አካላት የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱን መግለጫው ጠቁሟል፡፡

በተለያዩ ዓለማት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሚልኩት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ የብሔራዊ ባንክን መመሪያ በሚጥስ ሁኔታ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያስከትሉ የቆዩ ሕጋዊ ፈቃዳቸው በፈጸሙት ተደጋጋሚ ጥፋት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተሰረዘባቸው ዓለም አቀፍ የሃዋላ አስተላላፊዎችና ሕገ-ወጥ የሃዋላ ድርጅቶችም እርምጃው የተወሰደባቸው ናቸው ብሏል።

በተጨማሪም በሀገር ውስጥ ሕገ- ወጥ የውጭ ምንዛሪ ማስተላለፊያ መተግበሪያዎችን በመጠቀም ሀብትን ከሀገር በማሸሽ ላይ ያሉ ድርጅቶች ባለቤቶችም በቁጥጥር ሥር ውለዋል ነው ያለው።

የብሔራዊ ባንክ ሕግን በሚጥስ ሁኔታና ያለምንም ፈቃድ የክሪፕቶ ከረንሲ መተግበሪያን በመጠቀም በሕገ- ወጥ መንገድ የውጭ ምንዛሪን ሲያዘዋውሩ የነበሩ አካለት ላይም እርምጃ መወሰዱንም መግለጫው አመልክቷል፡፡

በሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም ላይ በማነጣጠር ሲፈጸም የነበረው ኢኮኖሚያዊ አሻጥር ትላልቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶችን ለማስተጓጎል፤ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ቅሬታ እንዲያድርበት እንዲሁም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዳያንሰራራ በተቀናጀ መንገድ ሲፈጽሙት የነበረ መሆኑንም አንስቷል፡፡

የሀገርን ደኅንነት ስጋት ላይ በሚጥሉ እና የሀገርን ኢኮኖሚ በሚጎዱ አሻጥሮች ላይ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን በመከታተል የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ የተጀመረው የተቀናጀ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በመግለጫው፥ መላው ሀገር ወዳድ ዜጋ መሰል ወንጀሎችንና ወንጀለኞችን በማጋለጥ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review