ባለፉት አራት ዓመታት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ከ500 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል

You are currently viewing ባለፉት አራት ዓመታት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ከ500 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል

AMN ህዳር 1/2018

ባለፉት አራት ዓመታት በውጭ ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ከ500 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።ዜጎች ከህገ ወጥ ጉዞ ራሳቸውን እንዲጠብቁም አሳስቧል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በተለያዩ አገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው የመመለሱ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አመልክቷል።

ከውጭ ግንኙነት ቁልፍ ሥራዎች አንዱ የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ መሆኑን የገለጸው ሚኒስቴሩ፥ በፖሊሲው አማካኝነት በውጭ አገር የሚኖሩ ዜጎቻችን መብት የማስከበር፣ ለዜጎች ተገቢ የቆንስላ አገልግሎት የመስጠት፣በሄዱበት ሀገር ህጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸውና የሀገሩ መንግሥት ዜጎቻችን ሀገራቸውን እንዲለቁ ሲወስን መብታቸው፣ ክብራቸውና ደህንታቸው ተጠብቆ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል።

በዚህም መሠረት ባለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ የመካከለኛ ምስራቅ፣የአፍሪካ እና እንደ ማይናማር ያሉ የእስያ ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ከ500 ሺህ በላይ ዜጎቻችንን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን ጠቁሟል።

ከመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ በሳዑዲ አረቢያ በተለያዩ እስር ቤቶችና ማቆያ ማዕከላት የሚገኙ ከ17 ሺህ በላይ ዜጎቻችን መመለስ መቻሉንና በአሁኑ ወቅትም በሳዑዲ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች የመመለሱ ሥራ መቀጠሉን በመግለጫቸው ላይ ተመላክቷል።

በተመሳሳይ በየመን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ 36 ዜጎች ወደሀገራቸው እንዲመለሱ የተደረገ ሲሆን ሌሎችንም አስፈላጊውን የሰነድ ማጣራት በማድረግ የጉዞ ሰነድ በማዘጋጀት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እንዲሁም ከዓለም ዓቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

በማይናማር፣ላኦስ እና ካምቦዲያ እንዲሁም በሌሎች ሀገራት በተመሳሳይ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎቻችን የመመለስ ጥረት መቀጠሉንም እንዲሁ።

ሆኖም ግን አሁንም ድረስ ዜጎች በተሳሳተ መረጃ በሕገ-ወጥ ደላሎች ተታለው ወደ ተለያዩ ሀገራት በመጓዝ ለእስራት እና ለሞት እየተዳረጉ መሆኑንና መንግሥት ዜጎች ከህገወጥ ጉዞ ራሳቸውን እንዲከላከሉ እና እንዲጠነቀቁ ነው ሚኒስቴሩ ያሳሰበው።

ወደ ውጭ ሃገራት የሚደረጉ ጉዞዎችና የስራ ቅጥሮች በህጋዊና መንግስት ባስቀመጠው አሰራር ብቻ ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review