የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሐዋላ ሥርዓትን ለማጠናከርና የፋይናንስ ተአማኒነትን ለመጠበቅ የሚያስችል የተቀናጀ እርምጃ ወሰደ

You are currently viewing የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሐዋላ ሥርዓትን ለማጠናከርና የፋይናንስ ተአማኒነትን ለመጠበቅ የሚያስችል የተቀናጀ እርምጃ ወሰደ

AMN- ህዳር 1/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የሕግ አስከባሪ አካላት ጋር በመተባበር፣ ባልተፈቀዱ የውጭ የሐዋላ ገንዘብ ማስተላለፍ ሥራዎች ላይ በተሰማሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ የተቀናጀ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሐዋላ ሥርዓትን ለማጠናከርና የፋይናንስ ተአማኒነትን ለመጠበቅ የሚያስችል የተቀናጀ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

እነዚህ እርምጃዎች የኢትዮጵያን የፋይናንስ ሥርዓት በመጠቀም ድንበር ዘለል የገንዘብ ማስተላለፍ ተግባራትን በሚፈጽሙ ደላሎችና ገንዘብ አቅራቢዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድን እንደሚያካትቱ ገልጿል፡፡

ይህ እርምጃ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ሥርዓትን ተአማኒነት ለመጠበቅና የውጭ ምንዛሪ ፍሰት በሕጋዊ፣ ግልጽና መደበኛ በሆኑ መንገዶች መከናወኑን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት የሚያንጸባርቅ መሆኑን አመልክቷል፡፡

በመሠረቱ፣ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውሮችን ለመፈጸም መደበኛ የፋይናንስ ሥርዓትን መጠቀም የውጭ ምንዛሪ ገበያን ተአማኒነት የሚያኮስስና የሀገሪቱን የገንዘብ ሥርዓት አደጋ ላይ የሚጥል አካሄድ እንደሆነም ነው የገለጸው፡፡

በአንጻሩ፣ እነዚህ የማስተካከያ እርምጃዎች ሕገ ወጥ የሐዋላ ዝውውርን ለመከላከል የሚደረግ ጥረት አካል መሆናቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡

ባንኩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን የፋይናንስ ሥርዓት ላልተገባ ዓላማ ለመጠቀም የሚፈልጉ አካላትን በመለየት ተገቢ እርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥልም አረጋግጧል፡፡

እንዲሁም፣ ባንኩ የውጭ ሐዋላ ፍሰት መደበኛ አካሄድን ተከትሎ እንዲፈጸም የሚረዱ እርምጃዎችን ለማጠናከርና በባንኮችና ሕጋዊ ፈቃድ ባላቸው የገንዘብ አስተላላፊዎች አማካይነት በቂና ቀጣይነት ያለው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት መኖሩን ለማረጋገጥ ተግቶ እንደሚሰራም አስገንዝቧል፡፡

እነዚህ የባንኩ ጥረቶች የሐዋላ ፍሰት ተደራሽ፣ ቀልጣፋና ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲፈጸም ለማድረግና የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መረጋጋትና የልማት ግቦች ለማሳካት የታለሙ መሆናቸውንም ነው ያመላከተው፡፡

በመሆኑም፣ ሕዝቡ ሕጋዊ የውጭ ሐዋላ አገልግሎት አቅራቢዎችን ለይቶ ማወቅ ይችል ዘንድ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕግን ተከትለው በውጭ ምንዛሪ ገበያ እንዲሳተፉ የተፈቀደላቸውን

የሐዋላ አስተላለፊ ድርጅቶችን ስም ዝርዝር በድረ ገጽ አድራሻ ማለትም በhttps://nbe.gov.et/mia/ አስቀምጧል፡፡

በመጨረሻም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕጋዊ የገንዘብ ማስተላለፊያ ዘዴዎችን አጠቃቀም የሚያበረታታና ሕዝቡ በፋይናንስ ሥርዓት ላይ ያለውን ተአማኒነት የሚያጠናክር ደህንነቱ

የተጠበቀና ጠንካራ/ምቹ የፋይናንስ ከባቢ ለመፍጠር ቁርጠኛ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review