ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የኢፌዴሪ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን አከባበር በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
የምስረታ በዓሉን በተመለከተ የሚካሄደውን የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ በተመለከተም የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዓለም አየሁ አሰፋ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር ስለሺ ስህን እና የኦሮሚያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንተርናሽናል ኢንስትራክተር ሽመልስ ዳዊት መግለጫ ሰጭተዋል።
የኢፌደሪ አየር ኃይልን 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል “የኢትዮጵያ አየር ኃይል የአንድነትና የነፃነት ምልክት” በሚል መሪ ሀሳብ ይከበራል።
የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በመግለጫቸው፤ አየር ኃይል በ90 ዓመት ታሪኩ የመውጣትና የመውረድ አጋጣሚዎችን ማስተናገዱን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከብዙ የዓለም ሀገራት በፊት የአየር ኃይል፣ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ ባንክና መሰል ዘመናዊ የመንግስት አገልግሎት መስጠት የጀመረች ታላቅና ጥንታዊት ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ናት ስንል በምክንያት ነው ያሉት ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፤ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ኢትዮጵያ ከገነባቻቸው ሥመ ገናና ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢፌዴሪ አየር ኃይል ባሳለፋቸው 90 ዓመታት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅ የሚያስችል ተግባር ሲፈፅም መቆየቷ ብለዋል።
አየር ኃይሉ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል በደምና በአጥንታቸው ሀገር ያጸኑ ጀግኖቻችን ያፈራ መሆኑን ገልጸዋል።
በ90ኛ ዓመቱ ክብረ በዓል ላይ ሀገርን በመጠበቅና ሉዓላዊነትን በማስከበር ያከናወነውን ስራ ለህዝብ እይታ ክፍት ይደረጋል ብለዋል።
የኢፌዴሪ አየር ሀይል አቅሙን በሰው ሀይል ልማት፣ በውጊያ መሰረተ ልማትና በትጥቅ በማሟላት ኢትዮጵያን የሚመጥን ተቋም እየተገነባ መሆኑን ገልጸዋል።
የዘንድሮው የምስረታ ክብረ በዓል በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ያለ ድባብ እንዲኖረው ታስቦ እንደሚከበር ገልጸው፤ “ለኢትዮጵያ አየር ሀይል በሙሉ አቅሜ ሮጣለሁ” በሚል መሪ ሀሳብ 10 ኪሎ ሜትር ሩጫ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
ሩጫው በየዓመቱ ቋሚ ሆኖ የሚቀጥል መሆኑን በመጥቀስ በሩጫው ሁሉም መሳተፍ እንደሚችል ጠቁመዋል።
ከዚህም ባሻገር የምስረታ በዓሉ በኮንፍረንስ፣ ኤክዚቢሽንና በአየር ትርኢትና መሰል ተግባራት በድምቀት ይከበራል ነው ያሉት።
የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዓለምአየሁ አሰፋ፤ ኢትዮጵያ ሀገራቸውን በጀግንነት ያስከበሩ ዜጎች ምድር መሆኗን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማስከበር ደግሞ የኢፌዴሪ አየር ኃይል የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል ብለዋል።
በቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር የሚካሄደው የኢፌዴሪ አየር ኃይል የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ ለከተማዋ ዕድገት የጎላ አበርክቶ እንዳለው ገልጸዋል።
የኢፌደሪ አየር ኃይል በዚህ መገኘት የከተማዋን ተፈላጊነትና ተመራጭነት አሳድጎታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር ስለሺ ስህን በአየር ኃይል 10 ኪሎ ሜትር ሩጫ ዓለም አቀፍ ውድድር መሆኑን መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በውድድሩ ከጎረቤት ሀገራት ጭምር የሚሳተፉ ዓለም አቀፍ አትሌቶች እንደሚኖሩ ገልጸው፣ ለውድድሩ አሸናፊዎች እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር ሽልማት ተዘጋጅቷል ብለዋል።