የታሪክ ተመራማሪና መምህር ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌ.ዴሌቦ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

You are currently viewing የታሪክ ተመራማሪና መምህር ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌ.ዴሌቦ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

AMN ህዳር 2/2018

የታዋቂው የታሪክ ተመራማሪና መምህር ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌ.ዴሌቦ የቀብር ስነ ስርዓት ዛሬ በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ-ክርስቲያን ተፈጽሟል።

በቀብር ስነ ስርአቱ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች ፣የፕሮፌሰር ላጲሶ ቤተሰቦች እና ወዳጅ ዘመዶች ተገኝተዋል።

በቀድሞው በከንባታ እና ሐዲያ አውራጃ በኩፋላ ሐበሌ ግንቦት 12 ቀን 1930 ዓ.ም የተወለዱት ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌ.ዴሌቦ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በቢቾ ሆሳዕና ሚሽን ትምህርት ቤት ፣የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ አዳማ በሚገኘው የአፄ ገላውዴዎስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ባይብል አካዳሚ ተከታትለዋል።

በፍልስፍና እና በታሪክ ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ድረስ ትምህርታቸውን በአሜሪካን ሀገር ተከታትለዋል።

በኋላም የፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝተው፤ለሁለት ዓመታት በቨርጂኒያ ዩንየን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሲያስተምሩ ቆይተዋል።

የ1966 ዓ.ም የኢትዮጵያ አብዮት ተከትሎ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው፤ በታሪክ ምርምር እና በማስተማር አገራቸውን አገልግለዋል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ጥናት የራሳቸውን አሻራ ያሳረፉት ፕሮፌሰሩ ለኢትዮጵያ ታሪክ እድገት አስተዋጽኦ ያበረከቱ መጻሕፍትን አበርክተዋል።

የኢትዮጵያ ረጅም የሕዝብና የመንግሥት ታሪክ ፣.የኢትዮጵያዊነት ታሪካዊ መሰረቶችና መሳሪያዎች ፣የቀይ ባሕርና የዓባይ ሸለቆ ሚና እንዲሁም አጭር የጌዴኦ ህዝብ ታሪክን ጨምሮ በርካታ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያተኮሩ መጻሕፍትን ጽፈዋል።

ህብረ ብሄራዊ አንድነት እንዲጎለብት የሚያግዙ በርካታ የምርምር ሥራዎችንም አከናውነዋል።

የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌ.ዴሌቦ ባለትዳር እና የሦስት ሴት ልጆች አባት የነበሩ ሲሆን፤ ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ87 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review