ትርክታችንን የምናስተካክለው እኛው ነን

You are currently viewing ትርክታችንን የምናስተካክለው እኛው ነን

‎AMN ህዳር 02/2018 ዓ.ም

‎በኢትዮጵያ የተመሰጠው ጋናዊው ዎዴ ማያ ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተዘዋውሮ ”በቴሌቪዥን የማታዩት አፍሪካ” በሚል ርዕስ ዘለግ ያለ ዘጋቢ ፊልም አዘጋጅቷል፡፡  ቅኝቱን ከአዲስ አበባ የጀመረው ወጣቱ ጋናዊ ወቅቱ የእንቁጣጣሽ በዓል ስለነበር የኢትዮጵያዉያን አዲስ ዓመት ለምን ከሌላው በተለየ ወቅት ላይ ይከበራል ሲል ይጀምራል፡፡

‎ኢትዮጵያዊያንን በማነጋገር ምላሹን ያገኘው ወጣቱ ዩቲዩበር ለየት ባለው የዘመን አቆጣጠር ተደንቆ ሳያበቃ ከ80 በላይ ቋንቋዎች የሚነገርባት ኅብረ ብሔራዊት ሀገር መሆኗን ይረዳና ይበልጥም ይደማማል፡፡ ወዲህ እጅግ ያማሩ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች፣ መናፈሻዎች እና ፓርኮችም ቀልቡን ገዝተው የእውነት ያለሁት በአፍሪካ ምድር ነውን ሲል እራሱን ይጠይቃል፡፡

‎አዲስ አበባ ቆንጅታለች፣  በፍጥነት የሚሰሩ መሠረተ ልማቶች እጅግ አስገራሚ ናቸው ካለ በኃላ የሆነ ቦታ ደርሰሼ ስመወስ እንደፈንድሻ ፈክታ ትጠብቃለች  እያለ መዲናዋን ያሞካሻታል ፡፡እውነትም አዲስ አበባ እንደ ስሟ  ናት ሲል ለአድናቆቱ ቃላት እያጠሩት ሌላ መልክ፣ ደሞ ሌላ ውበት ይመለከታል፡፡

‎ላፉት 6 ዓመታት ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን የሚገልፀው ጋናዊው ወጣት በነዚህ አመታት የመጣው ፈጣን ለውጥ በቃላት ሊገለጽ የሚችል አይደልም ይላል፡‎ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ወደ ተገነባበት ሥፍራ ያቀናው ማያ ዎዴ፣ ይህ ደግሞ ሌላ ተዓምር ነው ይለናል፡፡ የግድቡ ታላቅነት የኢትዮጵያን ታላቅነት አመላካች መሆኑን ያነሳና በግድቡ የምህንድስና ጥበብም መደነቁን ይናገራል፡፡

‎በራስ አቅም የመገንባቱ ጉዳይ ደግሞ ሌላ ትልቅ መልዕክት ያዘለ መሆኑን በአፅንዖት ይገልፃል፡፡ ወደ ደቡብ የኢትዮጵያ ክፍል ያቀናና በዚያ የተደመመበትን ውብ ባህል በዘጋቢ ፊልሙ አካቷል፡፡

‎አፋር ክልልም ተጉዞ ነጭ ገነት ሲል የገለጸውን የጨው ምድር እና ልዩ ስሜት የሚያጭረውን እሳት ገሞራም ተመልከቱ ሲል ለዓለም አቅርቧል፡፡ ኢትዮጵያዊያን የተዋሀዱበት እና የቅኝ ግዛት ወራሪዎችን በአንድነታቸው ድል ያደረጉበት የጥቁር ህዝብ የኩራት ስፍራም ይህ ነው ሲል የአድዋ ተራሮችን አስመልክቷል፡፡

‎ቀደምት የሥልጣኔ ባለቤት መሆኗን ከሚመሰክሩት መካከል አንዱ የሆነውን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና ሌሎችንም ተዟዙሮ የተመለከተው ጋናዊው ወጣት በኢትዮጵያም በአፍሪም ሀብት ፊቱ ላይ በግልፅ በሚነበብ መደመም ሲደመም ይስተዋላል፡፡ ‎የድንቅ ተፈጥሮ መገኛ ወደ ሆነችው ጅማ አቅንቶም በኢትዮጵያ ስለተገኘው ቡና ግንዛቤ አግኝቶ ሌላውንም በዘጋቢ ፊልሙ ያስገነዝባል ዎዴ ማያ፡፡

‎ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ ናት ሲባል ሰምቷል፡፡ አሁን ግን በአካል የሰው ልጅ (ሉሲ) የተገኘበችትን የአፋር ምድር መርገጥ በመቻሉ ደስታው እጥፍ ድርብ ነው፡፡ በዓለም ዙሪያ ቢፈለግ አይገኝም የሚባልለትን እጅግ አስደናቂውን የባሌ ተራሮችን ንፁህ አየር እየቀዘፈ በሀሰት ተራማምዶ ከአናቱ ላይ ደርሷል፡፡

‎በዘጋቢ ፊልሙ ብዙ ውበት ፣ ብዙ ልማት፣ ብዙ ቆንጆ ባህል እና ድንቅ ተፈጥሮን የተመለከተው ወጣቱ ጋናዊ አሁን አፍሪካዊያን በድንበር መታጠርን ትተው የራሳቸውን አህጉር እየተዘዋወሩ የሚጎበኙበት ወቅት ሊሆን እንደሚገባ ይሞግታል፡፡ ሌሎች አፍሪካ ላይ ጭነው የቆዩትን የተዛባ ትርክት ማስተካከል የምንችለው እኛው አፍሪካዊያን ነን የሚለው ዎዴ ማያ የዚህ ዘጋቢ ፊልም ዋና ዓላማም ይሄው መሆኑን ገልጿል፡፡

ማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review