የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ከህዳር 2 እስከ ህዳር 11/2018 ዓ.ም ድረስ የሚኖረውን የአየር ሁኔታ አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ይፋ አድርጓል፡፡
በሚቀጥሉት የህዳር ወር የሁለተኛው ሳምንት አሥር ቀናት፣ በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት በቦረና፣ በምስራቅ ቦረና፣ በምዕራብ ጉጂ እና በጉጂ ዞኖች፤ የሲዳማ ክልል ዞኖች፤ የሶማሌ ክልል ደቡባዊና ደቡብ ምስራቅ ዞኖች እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡባዊ ዞኖች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች እንደሚጠቁሙ ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ አክሎም፣ በተለይም ከሳምንቱ አጋማሽ በኋላ አልፎ አልፎ በሚኖሩት ቀናት የሰሜን፣ የመካከለኛው፣ የምዕራብና የደቡብ ጎንደር ዞኖች፣ ባህርዳር ዙሪያ፣ አዊ፣ በምዕራብና ምስራቅ ጎጃም፤ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል፣ አሶሳ፣ ካማሺ እና የማኦኮሞ ልዩ ዞን፤ አርሲ እና ምዕራብ አርሲ፤ ባሌ እና ምስራቅ ባሌ ዞኖች ላይ አልፎ አልፎ ወቅቱን ያልጠበቀ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ አመላክቷል፡፡
ስለሆነም በሚኖሩት የብራ ቀናት ውሰጥ የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ አስፈላጊ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳስቧል፡፡
በሌላ በኩል በመካከለኛዉ፣ ምሥራቅ፣ ሰሜን እና የደቡብ ደጋማ ቦታዎች ላይ የለሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ እንደሚሄድ የትንበያ መረጃዎች እንደሚጠቁሙ ኢንስቲትዩቱ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡