የፖለቲካ ጥቅምን ለማስከበር አግባብነት በሌለዉ መንገድ ከሌሎች ሀገራት ጋር መወገን እንደ ሀገር ክህደት ይቆጠራል

You are currently viewing የፖለቲካ ጥቅምን ለማስከበር አግባብነት በሌለዉ መንገድ ከሌሎች ሀገራት ጋር መወገን እንደ ሀገር ክህደት ይቆጠራል

AMN- ሕዳር ዐ3/2018 ዓ.ም

የግልና የአንድን ቡድን የፖለቲካ ጥቅምን ለማስከበር አግባብነት በሌለዉ መንገድ ከሌላ ሃገር ጋር መወገን እንደ ሀገር ክህደት እንደሚቆጠር የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አቶ አያና ቡሊ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናገሩ፡፡

አቶ አያና አክለውም፣ ሀገራዊ እሳቤ ሲጠነክር ሀገራዊ ጥቅምን ለማስከበር ፍላጐት፣ አቅም እና ተግባቦትን በማጐልበት በጋራ መቆም እንደሚጠይቅ አብራርተዋል፡፡

ማንኛውም ሀገር በግንኙነት ውስጥ ትኩረት የሚሰጠው የሀገር ጥቅም ላይ ነው ያሉት የፖለቲካ ተንታኙ፤ ሁሌም የውስጡን በምናይበት እይታ የውጪውን ግንኙነት ማየት የለብንም ብለዋል፡፡

በሀገር ውስጥ ፖለቲካ ፍትህ፣ ዲሞክራሲ፣ የግለሰብና የቡድን መብት መከበር ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ ዓለም አቀፋዊ ሲሆን ሉአላዊነት እና የሀገር ጥቅምን ባስቀደመ መልኩ የሚሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ሀገርን የሚመራ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሉአላዊነትን እና የሀገርን ጥቅም ባስከበረ መልኩ ሊሰራ እንደሚችል የገለፁት የፖለቲካ ተንታኙ፤ እንደ ግለሰብና ቡድን ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚስተዋል አግባብነት የሌለዉ ወገንተኝነት እንደ ሀገር ክህደት ይቆጠራል ብለዋል፡፡

አንዳንድ ቡድኖች የፖለቲካ ጥቅማቸውን ለማስከበር ሌሎች ሀገራት ጋር መስራት ህጋዊ ይመስላቸዋል፤ ይህም ፖለቲካ በውስጥና በውጭ ያለውን ልዩነት ካለማወቅ የሚመነጭ ችግር ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሀገርን አንድነት ለመሸርሸር የሚሰሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ቢኖሩም ህዝቡን ከሚያለያዩትና ከሚያገፋፉት ነገሮች ይልቅ የሚያስተሳስሩት እንደሚጠነክሩ ብዙ አመላካች ነገሮች መኖራቸውን አንስተዋል፡

አቶ አያና አክለውም፣ ባለፉት 29 አመታት ውስጥ የሀገሪቱ የፖለቲካ መዋቅር አስተሳሰብ፣ ምልከታና ትኩረት በብሄርና በብሄረሰቦች ላይ ብቻ ያተኮረ እንደነበር ገልፀዋል፡፡

እንደ ሀገር ፌዴራላዊ ሥርዓትን በመከተል የማህበረሰብ፣ የብሄርና ብሔረሰቦችን ጥያቄ፣ የተዛቡ ግንኙነቶችን እና መብቶችን ማስከበር ትክክል ሆኖ ሳለ፣ ሀገራዊ አንድነት ላይ ያለው እሳቤ የተቀዛቀዘ እንዲሆን አድርጎት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከላፉት የለውጥ አመታት ወዲህ ባሳየችው መነቃቃት ያስመዘገበችው ውጤት፣ የእድገቷን መዳረሻ አመላካች ነው ያሉት የፖለቲካ ተንታኙ፣ በቅርቡ ለፍሬ የበቃው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና የጋራ የሆነው የባህር በር ጥያቄ ህዝቡ ሀገራዊ ጥቅምን ለማስከበር በአንድነት ስለመቆሙ ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review