ኢትዮጵያ የባህር በር አጥታ በቆየችባቸዉ ዓመታት ከባህር በሩ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ባታገኝም የባህር በሩ አደጋ ግን አላጣትም ሲሉ ምሁራን ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የቢዝነስና ስትራቴጂ መምህርና ተመራማሪዉ ጫልቺሳ አመንቴ (ዶ/ር) ከኤኤምኤን ፕላስ ጋር በነበራቸዉ ቆይታ እንደተናገሩት ቀይ ባህር ከኢትዮጵያ ድንበር በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት አቅራቢያ እንደመገኘቱ መጠን ባህሩ አጋጣሚ ሆኖ ቢሞላ ዉሃዉ ኢትዮጵያ ከመድረስ የሚያግደዉ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከታሪክ፤ ከአለም አቀፍ ህግና በባህር በር አቅራቢያ እንደመገኘቷ መጠን የባህር በር አጥታ ተዘግታ መቀመጥ አልነበረባትም ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የባህር በር እንዳታገኝ የሚፈልጉ አንዳንድ ሃገራት ለኤርትራ፤ ለጅቡቲ አልያም ለአፍሪካዊያን አስበዉ አይደለም፡፡

በኢኮኖሚ ያደጉ አንዳንድ ሃገራት የሌላዉን ሃገር ሃብት እንደራሳቸዉ ሃብት የሚመለከቱ በመሆኑ የራሳቸዉን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ሲሉ ሌሎች ሃገራት የባህር በር እድል እንዳያገኙ ያደርጋሉ ሲሉ ነዉ ያብራሩት፡፡
ኢትዮጵያ ግን በተፈጥሮም ሆነ በአለም አቀፍ ህግ መሰረት የባህር በር የማግኘትም ሆነ የመጠቀም መብት አላት፡፡
ኢትዮጵያ የባህር በር በማጣቷ ለወደብ ኪራይ ከፍተኛ ወጪ እንደምታወጣ የገለጹት ጫልቺሳ አመንቴ (ዶ/ር) ይህም በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የባህር በር ጉዳይ የወጪና የገቢ ምርቶች ጉዳይ ብቻም አይደሉም የሚሉት ተመራማሪዉ በተለይ ከሃገራዊ ደህንነት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠዉ የሚገባዉ ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በቀጣናዉ ከሚታየዉ ጂኦፖለቲካል እንቅስቃሴ አንጻር ሌላ ሶስተኛ ወገን በኢኮኖሚዉም ሆነ በደህንነት ጉዳይ ጣልቃ ቢገባ ለሃገሪቱ ከፍተኛ ስጋት ሊሆን እንደሚችል ነዉ የገለጹት፡፡ ይህም የባህር በር ጉዳይ የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የደህንነትና የሉአላዊነት ጉዳይ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነዉ ብለዋል፡፡
አለም አቀፍ ህጎች በኢኮኖሚ ያደጉትን ሃገራት ብቻ የሚያገልግሉ በተቀራኒዉ ደግሞ በማደግ ላይ ያሉ ሃገራትን ያገለሉ አለመሆናቸዉን የሚገልጹት ጫልቺሳ አመንቴ (ዶ/ር) የባህር በር ጉዳይ ከፍትህ አንጻር የሚቃኝ በመሆኑ የባህር በር ጥያቄዉ በዚሁ አግባብ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የባህር በር ሊኖራት ይገባል ሲሉ ያነሱት ሃሳብ አግባብነት ያለዉ በመሆኑ ኢትዮጵያ ህፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ የተነጠቀችዉን የባህር በር ያሉትን አማራጮች በመጠቀም መልሳ ልትጠቀምበት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ