የአፍሪካ የመንገድ ደህንነት ቀን ህዳር 7 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ አድዋ ድል መታሰቢያ ይከበራል።
የመንገድ ደህንነት ቀን ሁነት በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ስር በሚገኘው የአፍሪካ የመንገድ ደህንነት ኢኒሼቲቭ፣ የኢፌዴሪ የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር፣ የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት እና የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን(ኢሲኤ) የጋራ ትብብር የተዘጋጀ ነው።
የአፍሪካ ህብረት እ.አ.አ 2012 ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ቀኑ በየዓመቱ የሚከበር ሲሆን ከዓለም የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች መታሰቢያ ቀን ጋር የተሳሰረ መሆኑም ተመላክቷል።
ቀኑ በትራፊክ አደጋ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ እና የተጎዱ ሰዎች የሚታሰቡበትና በአፍሪካ ደረጃ የመንገድ ደህንነትንና ዘላቂ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን ለማረጋገጥ ሀገራት የጋራ ቁርጠኝነታቸውን የሚገልጹበት ነው።
አፍሪካ ከፍተኛ የትራፊክ አደጋዎችን ከሚያስተናግዱ አህጉራት መካከል አንዷ መሆኗን የአፍሪካ ህብረት ገልጿል።
ከዓለም ተሽከርካሪዎች ውስጥ ከአራት በመቶ በታች የሚገኝባት አፍሪካ የዓለም 25 በመቶ ገደማ የትራፊክ አደጋ ሞት እንደሚመዘገብባት አመልክቷል።
ከሚጎዱት መንገደኞች፣ የሳይክል እና ሞተር አሽከርካሪዎች መካከል አብዛኞቹ ወጣቶች መሆናቸውን ገልጾ የህብረቱ አባል ሀገራት በትራፊክ አደጋዎች ምክንያት ሁለት በመቶ የሚሆን ዓመታዊ ጥቅል ምርታቸው (ጂዲፒ) ወጪ እንደሚያደርጉ ነው ሀብረቱ ያስታወቀው።
ቀኑ በአፍሪካ የመንገድ ደህንነት የድርጊት መርሃ ግብር (ከእ.አ.አ 2021 እስከ 2030 የሚቆይ) ጥላ ስር የተቀናጀ የተግባር ምላሽ እና አጋርነትን የማጠናከር ግብ እንዳለውም ተመላክቷል።
በመንገድ ደህንነት ቀን የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች የሚታወሱ ሲሆን ሀገራት እ.አ.አ በ2030 የትራፊክ አደጋ ሞትን በ50 በመቶ ለመቀነስ የገቡትን ቃል ለማደስ የፖለቲካ ቁርጠኝነታቸውን ይገልጻሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የአፍሪካ የመንገድ ደህንነት ኢኒሼቲቭ በመረጃ ላይ የተመሰረተ የቁጥጥር ስርዓት ማጠናከርና በህብረቱ አባል ሀገራት “Safe System” የተሰኘ ዘመናዊ የመንገድ ደህንነት ስርዓት ማዕቀፍ የማስተዋወቅ ስራ እንደሚከናወን ከህብረቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።