ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 32) እንድታስተናግድ ተመርጣለች።
30ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 30) በብራዚል ቤለም እየተካሄደ ይገኛል። ኢትዮጵያ በስብሰባው ላይ ኮፕ 32ትን የማስተናገድ ጥያቄ በይፋ ያቀረበች ሲሆን የአፍሪካ ሀገራት ጉባኤውን እንድታስተናግድ ድጋፍ ሰጥተዋታል።
የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተደራዳሪዎች ቡድን ሊቀ መንበር ሪቻርድ ሙዩንጊ ቡድኑ የኢትዮጵያን የኮፕ 32 የማስተናገድ ጥያቄ ተቀብሎ ማጽደቁን ለኤኤፍፒ ገልጸዋል።
የኮፕ 30 ፕሬዝዳንት የሆነችው ብራዚልም የአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያን መምረጣቸውን አረጋግጣለች።

የተደራዳሪ ቡድኑ መደበኛ ያልሆነ ውሳኔ በሁሉም የጉባኤው ተሳታፊ ሀገራት መጽደቅ እንደሚጠበቅበት እና ይህም ኮፕ 30 በሚጠናቀቅበት ህዳር 12 ቀን 2018 ዓ.ም ይፋ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አስተናጋጅነት በድርጅቱ ስር ባሉ አምስት ቀጣናዎች ውስጥ ያሉ ሀገራት በመፈራረቅ የሚያዘጋጁት ነው።
ብራዚል የላቲን እና የካሪቢያን ሀገራት ወክላ መመረጧን ተከትሎ ኮፕ 30ን እያካሄደች ትገኛለች።
ኮፕ 30 እስከ ህዳር 12 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።