ብሔራዊ ባንክ በኢትዮጵያ የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎት እንዲሰጡ የተፈቀደላቸውን የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶችን ይፋ አደረገ

You are currently viewing ብሔራዊ ባንክ በኢትዮጵያ የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎት እንዲሰጡ የተፈቀደላቸውን የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶችን ይፋ አደረገ

AMN ህዳር 3/2018

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኢትዮጵያ የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎት እንዲሰጡ የተፈቀደላቸውን የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶችን ስም ዝርዝር ለሕዝቡ ይፋ አድርጓል።

በዚሁ መሠረት፣ ቀደም ሲል የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎት እንዳይሰጥ ታግዶ የነበረውና ዋና መስሪያ ቤቱ በአሜሪካ ቪርጂኒያ ግዛት በፎልስ ቸርች የሚገኘው ራማዳ ፔይ (ካህ) በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ አጠቃላይ ግምገማ ከተካሄደ በኋላ በሕጋዊ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ስም ዝርዝር ውስጥ ዳግም እንዲካተት መደረጉን ባንኩ በመግለጫው አመልክቷል።

ከዚህ ውሳኔ ላይ ሊደረስ የቻለው በሀገሪቱ ሕግና ደንብ መሠረት በድርጅቱ ላይ አስፈላጊው የቁጥጥርና የክትትል ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ መሆኑን ገልጿል።

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ አገልግሎት እንዳይሰጡ ታግደው የሚገኙ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች በሙሉ የሀገሪቱ ሕግና ደንብ የሚጠይቀውን መስፈርት ለማሟላት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ አሳስቧል።

የብሔራዊ ባንክ ዓላማ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች በግልጽነትና ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ብቻ እንዲሠሩ ድጋፍ ማድረግ እንደሆነ ነው ያስታወቀው።

በውጭ አገር የሚኖሩ ሰዎች ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ በሚያስተላልፉበት በማንኛውም ወቅት ሕጋዊና ግልጽ የሆነ አካሄድ መከተላቸውን ማረጋገጥ እንደሚኖርባቸው አስገንዝቧል።

ሕጋዊ ፈቃድ በተሰጣቸው የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች በኩል ገንዘብ መላክ ገንዘቡ ደህንነቱ ተጠብቆና ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርንና አሸባሪነትን በገንዘብ መደገፍን የሚጻረረውን አሠራር ተከትሎ ወደ ተቀባዩ እንዲደርስ እንደሚያደርግ ነው በመግለጫው ያመለከተው።

ሕዝቡ ፈቃድ የተሰጣቸው የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶችን ለይቶ ለማወቅ ይችል ዘንድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሕጋዊ ድርጅቶችን ስም ዝርዝር በድረ https://nbe.gov.et/mta/ ይፋ ማድረጉን ባንኩ ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕጋዊ የሐዋላ አገልግሎትን ለማበረታታትና የፋይናንስ ዘርፍን ጤናማ ዕድገት ለመደገፍ የሚረዳ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ግልጽና ቀልጣፋ የፋይናንስ ምህዳር እንዲኖር በትጋት መሥራቱን እንደሚቀጥል አስታውቋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review