ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ሀገራዊ አንድነት መጎልበት የኃይማኖት ተቋማት የላቀ ሚናቸውን አጠናክረው መቀጠል እንደሚጠበቅባቸው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀኃፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገለጹ።
“ሃይማኖቶች ለሰላም፣ ለአንድነትና ለአብሮነት” በሚል መሪ ሀሳብ 5ኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስ በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀኃፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ ለዘላቂ ሰላምና ለሕዝቡ አብሮነት መጠናከር የሃይማኖት ተቋማት የማይተካ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

ኮንፍረንሱ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና አብሮነትን ይበልጥ በማጠናከር ሁለንተናዊ እድገት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የሃይማኖት ተቋማትን ሚና ለማጎልበት ታልሞ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የሃይማኖት ተቋማት ለሰላም እሴቶች ግንባታ፣ ልማት እና ሀገራዊ አንድነትን አፅንቶ ለማስቀጠል ሚናቸው እንዲጎለብት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለውም ብለዋል።
በዚህም ተቋማቱ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ሀገራዊ አንድነት መጎልበት የላቀ ሚናቸውን ይበልጥ ማጠናከር የሚጠበቅባቸው መሆኑን አመልክተው፤ ሁሉም ዜጋ ለሰላም መፅናት የድርሻውን እንዲወጣም መልዕክት ማስተላለፋቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ኮንፍረንስ ከሁሉም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የሃይማኖት ጉባኤ አባላት፣ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የባህል መሪዎችና ሌሎች አካላት እየተሳተፉ ነው።