በትንሹ 20 ሰዎችን የጫነ የተርክዬ ወታደራዊ የጭነት አውሮፕላን በአዘርባጃን-ጆርጂያ ድንበር አቅራቢያ መከስከሱን የተርክዬ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የሃገሪቱ ባለስልጣናት እስከ አሁን የሟቾችን ቁጥር በይፋ ባይገልፁም፤ በአውሮፕላኑ የበረራ ሰራተኞችን ጨምሮ በትንሹ 20 ሰዎች ተሳፍረው እንደነበር ተሰምቷል፡፡
እንደ መከላከያ ሚኒስቴሩ ገለጻ፤ C-130 የተሰኘው የጭነት አውሮፕላን ከአዘርባጃን ወደ ተርክዬ በመጓዝ ላይ የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት በአደጋው ስፍራ የነፍስ አድን ስራዎች ተጀምረዋል፡፡
የጆርጂያ አቪዬሽን ባለስልጣን፤ አውሮፕላኑ ምንም አይት የአደጋ ጊዜ ምልክት ሳያሳይ ከራዳር መሰወሩን መግለጹን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የተርክዬ ፕሬዝዳንት ሬሴፕ ጣይብ ኤርዶጋን በበኩላቸው፣ በአደጋው የተሰማቸውን ሃዘን በመግለፅ ሟቾችን ሰማዕታት ሲሉ ገልጸዋቸዋል፡፡
የአዘርባጃን ፕሬዝዳንት ኢልሃም አሊዬቭ፣ ለቱርክዬ ፕሬዝዳንት እና ህዝብ በአደጋው የተሰማቸውን ሃዘን በመግለፅ መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡
በሊያት ካሳሁን