የጃፓን ገበያ በአዲስ አበባ

You are currently viewing የጃፓን ገበያ በአዲስ አበባ

AMN – ህዳር 4/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ቦሌ ጃፓን ኢምባሲ አካባቢ የሚገኘው ቻይና ገበያ በመባል የሚታወቅ የገበያ ማዕከል በመዲናዋ የሚኖሩ የተለያዩ ሃገራት ዲፕሎማቶች ተመራጭ የመገበያያ ስፍራና የአትክልት የገበያ ማእከል እየሆነ መጥቷል፡፡

አዲስ አበባ ባለ ብዙ ቀለም እና መልክ ያላት ከተማ ስትሆን ከተለያዩ የአለም ክፍሎች የመጡ ዜጎች የሚኖሩባት የአለማችን ሶስተኛዋ የዲፕሎማቶች መነሃሪያ ነች፡፡

እነዚህ የዉጭ ሃገር ዜጎች የተለያዩ ግብይቶችን ለመፈጸም ከሚገለገሉባቸዉ የገበያ ስፍራዎች አንዱ በቦሌ ጃፓን ኢምባሲ አካባቢ የሚገኘዉ የአትክልት የገበያ ማእከል ተጠቃሽ ነዉ።

በገበያ ማእከሉ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች እና ኢትዮጵያውያንም የሚገበያዩ ቢሆንም ፣ ከውጭ ሀገር ዜጎች መካከል የቻይና ዜግነት ያላቸው በብዛት ይገበያዩበታል፡፡

በዚህ የተነሳም በስፍራው በንግድ ላይ የተሰማሩት ነጋዴዎች የቻይንኛ ቋንቋን አቀላጥፈው በመናገር ንግዳቸውን ሲያቀላጥፉ ኤ ኤም ኤን በስፍራው ባደረገው የአዲስ ጓዳ ቅኝት አረጋግጧል።

ኤ ኤም ኤን ካነጋገራቸው የጃፓን ወይም ቻይና የአትክልት ገበያ ነጋዴዎች መካከል ሙባረክ አንዱ ሲሆን ፣ በማእከሉ የሚያቀርባቸው ምርቶች ጥራታቸዉን የጠበቁ እና የውጭ ሀገር ዜጎች አዘውትረው የሚጠቀሟቸው መሆኑን ገልጾ በግብይቱም ወቅት ደምበኞቹን በቻይንኛ ቋንቋ እያነጋገራቸው ንግዱን ያለ ቋንቋ ችግር እንደሚያሳልጥ ተናግሯል።

ጃፓን ገበያ የሚል ስያሜ ያገኘው በስፍራው የጃፓን ኢምባሲ ስለሚገኝ መሆኑን ነጋዴዎቹ ተናግረዋል፡፡

ከተገበያዮቹ መካከል አንዷ የሆነችዉ ኡማን የምትባል ህንዳዊት እንዳለችው፤ ጃፓን ገበያ ስትመጣ ይህ ለሁለተኛ ጊዜዋ መሆኑን ጠቅሳ፣ እዚህ ስፍራ የምትገበያየው የምትፈልጋቸው የግብርና፤ የእንስሳት ተዋጽኦና ሌሎች ምርቶችን በብዛትና በጥራት ስለምታገኝ መሆኑን ጠቅሳለች፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ለስድስት አመታት ያህል ኖሬአለሁ የምትለዉ ህንዳዊት ገበያተኛ መዲናዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየለማች፤ እያደገችና እየተቀየረች መሆኗን ገልጻለች፡፡

አንዳንድ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችና ተገበያዮች በበኩላቸዉ በገበያ ማእከሉ ሁሉም ዜጋ እንደሚገለገል በመጥቀስ ጃፓን የገበያ ማእከልን የሚመርጡት ትኩስና ጥራት ያላቸዉን የግብርናና የእንስሳት ተዋጽኦዎችን ስለሚያገኙ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review