ለሴካፋ ከ17 ዓመት በታች የእግርኳስ ውድድር በቂ ዝግጅት እንደተደረገ ተገለፀ

You are currently viewing ለሴካፋ ከ17 ዓመት በታች የእግርኳስ ውድድር በቂ ዝግጅት እንደተደረገ ተገለፀ

AMN – ህዳር 04/2018 ዓ/ም

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚከናወነው ከ17 ዓመት በታች የምስራቅ አፍሪካ ዞን (ሴካፋ) የእግርኳስ ውድድር አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

በኤልያና ሆቴል በተሰጠው መግለጫ ላይ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መኪዩ ሞሐመድ እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ተገኝተዋል።

አቶ መኪዩ ሞሐመድ ውድድሩ የሀገራችንን ገፅታ የምናሳይበት ስለሆነ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

ውድድሩ የተሳካ እና እኛም እንደሀገር ውጤታማ እንድንሆን ተሰርቷል ያሉት አቶ መኪዩ ድጋፉ እስከመጨረሻው እንደሚዘልቅ አረጋግጠዋል።

በተመሳሳይ የእግርኳስ ፌዴሬሽኑም ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ የገለፁት ፕሬዝዳንቱ አቶ ኢሳያስ ጂራ ውድድሩ በሁለት ከተሞች እንደሚከናወን ተናግረዋል።

ተሳታፊ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ ሙሉ ወጪያቸው በመንግስት እንደሚሸፈንም አቶ ኢሳይስ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ 10 ሀገራት የሚሳተፉበት ውድድር በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች ላይ ይከናወናል።

ኢትዮጵያ የምትገኝበት ምድብ አንድ ቡድኖች በአዲስ አበባ ፣ ምድብ ሁለት ላይ ያሉት ደግሞ በድሬዳዋ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በአዲስ አበባ የሚደረገው ጨዋታ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይደረጋል።

ጨዋታዎቹም 7 እና 10 ሰዓት ላይ ይከናወናሉ ተብሏል።

በድሬዳዋ ስታዲየም የሚከናወኑ የምድብ ጨዋታዎች ደግሞ 11 እና ምሽት 2 ሰዓት ላይ ይከናወናሉ።

የፊታችን ቅዳሜ የሚጀምረው ውድድር የቀጥታ ሽፋን እንዲያገኝ እየተሰራ እንደሚገኝ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ ተናግረዋል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review