ምድረ ቀደምትነትን ያደመቀው የቡና ፓርክ

You are currently viewing ምድረ ቀደምትነትን ያደመቀው የቡና ፓርክ

AMN- ህዳር 5/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ አሁን ላይ በተገበረችው እና እየተገበረችው ባለው የኮሪደር ልማት የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ የመዝናኛ እንዲሁም የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች መገንባታቸው ይታወቃል፡፡

ከእነዚህ በተጨማሪ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ቡና ፓርክ ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ ቡናን ከነክብሩ የሚያስተዋውቁ መሸጫ ሱቆች እና ካፌዎች ተከፍተዋል ፡፡

‎በቡና ፓርክ ሲገኙ ቡናን የሚያጣጥሙት አይነ ግቡ ሆነው ከተሰናዱ የኪነ-ጥበብ አሻራዎች ጋር ነው።

‎ቡና ፓርክ ለአይን የሚማርኩ ልብን የሚያሞቁ ገፅታዎችን የተላበሰ ከመሆኑ ባሻገር ከተለያዩ የኢትዮጰያ አከባቢዎች የሚመረቱ የቡና ምርቶች የሚያቀርቡ “ኮፊ ሀውሶች” መገኛ ጭምር እንዲሆን ተድርጎ የተሰራ ነው።

‎በስፍራው ባህላዊ የሆነው የምህንድስና ጥበብ ከዘመናዊ ጋር ተጣምሮ አካባቢው የተለየ ገፅታን እንዲላበስ ከማስቻሉም በላይ፣ በኢትዮጰያ ውስጥ ያሉ የቡና ዝያዎች የሚያሳዩ ችግኞች ፀድቀው ይታያሉ።

‎ሌላኛው የቡና ፓርክን ገፅታ ከሚያጎሉ ነገሮች መካከል አንዱ የዓለም ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን ሃውልት ሲሆን የብዙዎችን ቀልብ እንዲስብ አስችሎታል

የእኒህ ታላቅ ሰው ሀውልት በቡና ፓርክ መቆም፣ አዲሰ አበባ ከተማ ባለውለታዎችን በመዘከር ትውልዱ እንዲያውቃቸው ለማድረግ የሰራችው ስራ እንደሆነ ያመላክታል፡፡

‎በቡና ፓርክ ቡና ሲጠጡ ያገኘናቸው ዜጎችም ቦታው ላይ መገኘት ቡና ከመጠጣት በላይ ነው ሲሉ አጫውተውናል። ቦታው ንፁህ አየር ያለበት፣ ለአይን በሚማርክ ስፍራ በመሆኑ ከወዳጅ ዘመድ ጋር ቡና እየጠጡ ለማውጋት አመቺ መሆኑን ገልፀዋል ።

እንዲሁም በስፈራው ቡናን ከመጠጣት በዘለለ የቡና የአዘገጃጀት ስዓርት ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ያለውን ሂደት የሚያሳይ ስፍራ መሆኑን ነው ተጠቃሚዎች የገለፁልን።

‎የቡና ችግኝ ምን እንደሚመስል ለመረዳትም ዕድል እንዳገኙ ነው ተጠቃሚዎች የተናገሩት።

ከተማ አስተዳደሩ፣ በሀገራችን ቡና በማምረትና ወደ ውጭ በመላክ የሚታወቁ ተቋማት፣ ይህንን ደረጃውን የጠበቀ የቡና ፓርክ በማዘገጀት እንዲገለገሉበት እንዳደረገ ገልፀው፣ ቦታው ለከተማዋ ተጨማሪ ውበትና መልክም አጎናፅፏል ሲሉ ሃሳባቸውን አጋርተውናል ፡፡

‎በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review