ኩላሊት ዋና ተግባሩ በሰውነት ውስጥ ያለውን ውሃና ኬሚካል ሚዛኑን ማስጠበቅ ነው፡፡
በተጨማሪም የደም ግፊትን እና የደም አሲድ መጠንን ይቆጣጠራል እንዲሁም ቫይታሚን ዲ ሥራ እንዲጀምር እና ቀይ የደም ሴል ከአጥንት ውስጥ እንዲመነጭ ያግዛል፡፡
ኩላሊት በአንድ ቀን 1 ሺህ 5ዐዐ ሊትር ደምን የማጣራት አቅም ያለው ሲሆን፤ ኩላሊት ሲዘጋ እንኚህ ተግባርትን በማስተጓጎል ለከፍተኛ ጉዳት ይጋለጣል፡፡
በቅዱስ ጴጥሮስ ስፒሻላይዝድ ሆስፒታል የጠቅላላ ቀዶ ህክምናና የዬሮሎጂስት ስፒሻሊስት ሀኪም የሆኑት ዶ/ር አህመድ መሐመድ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ የኩላሊት መዘጋት የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩትም፤ በዋናነት ግን በሽንት ትቦ መስመር መዘጋት የሚከሰት ችግር ሲሆን ይህም ኩላሊትን ለከፋ አደጋ ሊያጋልጥ ይችላል ብለዋል፡፡
የኩላሊት ጠጠር በሽንት ትቦ ላይ ከተቀመጠና መንቀሳቀስ ካልቻለ፣ በኤንፌክሽን እና በአደጋ ምክንያት የሚመጣ የሽንት ትቦ መጥበብ ለኩላሊት መዘጋት መንስኤ ናቸው፡፡

በመሆኑም ከኩላሊት እስከ ሽንት ትቦ ድረስ ያለ ቀጭን መስመር ፣ የሽንት ፊኛ ጫፍ እና ከሽንት ፍኛ እስከ ሽንት መዉጫ ጫፍ ያለው መስመር ላይ የሚከሰት የመዘጋት ችግር ኩላሊትን ሊዘጋ እንደሚችል ነው ዶ/ር አህመድ የገለጹት፡፡
ሌላው የሽንት ፊኛ፣ የሽንት ቱቦ እና የኘሮስቴት ካንሰር እብጠት ሲፈጥር የኩላሊት መዘጋት ሊያስከትል ይችላል፡፡
በቀኝ ወይም በግራ ጐን ቀስፎ የሚይዝ ከፍተኛ ህመም ያለው ውጋት፣ ከ2 እስከ 3 ቀን የሚቆይ የማያስተኛ ከፍተኛ ህመም፣ የኩላሊት ጠጠር የዘጋው ከሆነ ወደ ሽንት ቱቦ ከፍተኛ ህመም ካለ አንድ ሰው በኩላሊት መዘጋት ህመም መጠቃቱን አመላካች ናቸው፡፡

በተጨማሪም የሽንት መደፍረስ፣ ደም የቀላቀለ ሽንት፣ ሽንት ሲሸኑ ማስማጥ፣ ማቃጠል እና ቶሎ ቶሎ መሽናት የህመሙ ምልክቶች ናቸው፡፡
ህመሙ ከ24 እስከ 48 ሰዓታት ከፍተኛ ይሆንና ከዚያ በኃላ ይቀንሳል፤ ቶሎ ካልታከመ እየቆየ ሲሄድ ኩላሊትን ከጥቅም ውጪ እስከማድረግ ይደርሳል፡፡
የኩላሊት መዘጋትን ቀድሞ ለመከላከል ሲትሪክ አሲድ ንጥረ ነገር ያላቸውን ምግቦች እንደ ሎሚ፣ ብርቱካንና ኩከንበርግን አዘውትሮ መመገብ እንዲሁም ሲጃራ ማጨስ፣ አልኮል መጠጣት፣ እና ጫት መቃምን በማቆም በሽታውን ከመከሰቱ በፊት መከላከል እንደሚያስችል ዶ/ር አህመድ መሐመድ አብራርተዋል፡፡
በበረከት ጌታቸዉ