የብሔርች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ኢትዮጵያዊ ማንነትን ከብሔር ማንነት ጋር ሚዛናዊ ለማድረግ ፋይዳው የጎላ መሆኑን በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽ/ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ በላይ ወዲሾ ገለጹ።
አቶ በላይ ህዳር 29 የሚከበረውን 20ኛው የብሔርች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀንን አስመልክቶ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ ከለውጡ በፊት ይስተዋል የነበረውን የነጠላ ትርክትን በማረቅ የወል ትርክትን ለማስረጽ የቀኑ መከበር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርአትን መከተል ከጀመረች ከሰላሳ አመት በላይ ያስቆጠረች ሲሆን፤ በብሔር ማንነት፣ በባህልና በቋንቋ ላይ ትኩረት ያደረገ ነጠላ ትርክት የሚያጎላ እንደነበር አስታውሰዋል።
የነጠላ ትርክትና የወል ትርክት ሚዛናቸውን ጠብቀው እስካልሄዱ ድረስ በሀገር ግንባታ ላይ የተዛባ ሁኔታን ይፈጥራል ሲሉም ተናግረዋል።
ቀደም ሲል የወል ትርክት ላይ እና ሀገራዊ ማንነት ላይ የጎላ ሥራ አለመሰራቱን የገለፁት አቶ በላይ፤ ሀገር በነጠላ ትርክት አይፀናም ሲሉ አስረድተዋል።

በዓሉ በሕዝቦች መካከል ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር፣ ዲሞክራሲያዊ አንድነት እንዲጠናከር እና ህብረብሔራዊ አንድነት እንዲጎለብት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋልም ብለዋል፡፡
የብሔርች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ባለፉት 19 ዓመታት ሲከበር የብሔር ብሔረሰቦችን ባህል፣ ቋንቋ፣ እሴትና ልዩ ልዩ መገለጫዎችን በማስተዋወቅ የእርስ በርስ ትስስርን ለማጎልበት የጎላ አስተዋፅኦ እንደነበረው ተናግረዋል።
20ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረብሔራዊ መግባባት” በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚከበር ይጠበቃል፡፡
በበረከት ጌታቸው