. ከ2008 ዓ.ም በፊት የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች ለምዝገባ ወደ ቴክኒክና ሙያ ቢያቀኑም መመዝገብ እንዳልቻሉ ገልጸዋል
. ትምህርት ፈላጊዎቹ በማንዋል እንዲመዘግቡ ለኮሌጆቹ ማሳወቁን ቢሮው ጠቁሟል
ወጣት አሰፋ ደመመው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ነዋሪ ነው፡፡ በ2007 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስዶ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም በመግባት በ2011 ዓ.ም በአግሪ ቢዝነስና ቫልዩቼን ማኔጅመንት የትምህርት መስክ የመጀመሪያ ድግሪውን እንዳገኘ ይናገራል፡፡
ከምርቃት በኋላ በተመረቀበት የስራ መስክ ስራ ማግኘት ባለመቻሉ የተሻለ ስራ የሚያገኝበትና በግሉም መስራት የሚችልበት የስራ መስክ ለመማር በመወሰን በንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ የትምህርት ዘርፍ ስልጠና ለመውሰድ መምጣቱን ይናገራል፡፡ ነገር ግን የመመዝገቢያ ሲስተሙ (ኢ-ስኩል) ከ2008 ዓ.ም በፊት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰዱትን መመዝገብ እንደማይችል፣ ለጊዜው ስምና ስልክ ቁጥራቸውን ሰጥተው፣ የአዲስ አበባ ከተማ ስራና ክህሎት ቢሮ ሲፈቅድ የሚመዘገቡ መሆኑን እንደተነገራቸውና እየተጠባበቁ እንደሆነ ወጣት አሰፋ ያስረዳል፡፡
የሙያ ስልጠናው በቅጥር አሊያም በግል መስራት የሚችልበትን እድል የሚያሰፋ መሆኑን የሚያነሳው ወጣት አሰፋ፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ክህሎት የሌላቸውን ሰዎች የሙያ ባለቤትና ስራ ፈጣሪ ለማድረግ የተቋቋሙ እንደመሆናቸው ችግሩ ተፈትቶ መማር የሚችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር ጠይቋል።
ሌላኛው አስተያየቱን ያጋራን በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ካዲስኮ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆነው ወጣት ሚኪያስ ብርሃነ ነው፡፡ የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን ያጠናቀቀው በ2007 ዓ.ም ሲሆን አክሱም ዩኒቨርሲቲ በመግባት በኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ድግሪውን ይዟል፡፡ በተማረበት የትምህርት መስክ እየሰራበት ባለመሆኑ ራሱን ለማሻሻል በማታው ክፍለ ጊዜ በደረጃ 4 በሀርድዌር ኔትዎርኪንግ ሰርቪስ የትምህርት መስክ በንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለመማር ቢያመለክትም፤ ሲስተሙ ከ2008 ዓ.ም በኋላ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ የወሰዱትን እንደማይቀበል እንደነገሩት ይገልፃል፡፡ “ስምና ስልክ ቁጥራችንን ሰጥተናል፤ የኮሌጁ ሬጂስትራር ኃላፊ ሳነጋግረው መፍትሔ እስኪመጣ ጠብቁ፤ እንደውላለን” የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ወጣት ሚኪያስ ነግሮናል፡፡
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ፋንቱ ተመስገን ይባላሉ፡፡ ልጃቸው (ወጣት ዮናታን ታሪኩ) የ12ኛ ክፍል ፈተናን በ2004 ዓ.ም ወስዶ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ያመጣ ቢሆንም በግል ችግር ምክንያት ወደ ዩኒቨርሲቲ አልገባም፡፡ አሁን ላይ ልጃቸው የሙያ ባለቤት በመሆን ስራ ሰርቶ የሚለወጥበት ሁኔታ ለመፍጠር በንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለማስመዝገብ ቢያቀኑም ማስመዝገብ እንዳልቻሉ ይናገራሉ፡፡
ከተመዝጋቢዎች የተነሱ ቅሬታዎችንና አስተያየቶችን በመያዝም የንፋስ ስልክ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የሚመለከታቸው ኃላፊዎችን ጠይቀናል፡፡ ወይዘሮ መስከረም አስፋው የንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የስልጠና እና አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ዲን ናቸው፡፡
ኮሌጁ በ2018 የትምህርት ዘመን በቀን፣ በማታ እንዲሁም ቅዳሜና እሁድ 1 ሺህ 625 ተማሪዎችን ለመቀበል አቅዶ ምዝገባ እያከናወነ ሲሆን (ይህ ጽሁፍ እስከተጠናቀረበት ህዳር 2 ቀን 2018 ዓ.ም) 1 ሺህ 219 ተማሪዎችን በሲስተም (E-School) በማስደገፍ መዝግቧል፡፡
ወይዘሮ መስከረም እንደገለፁት፣ በዋናነት የ2018 የትምህርት ዘመን የሚመዘገቡት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና ወስደው የመግቢያ ነጥብ ያላመጡ ተማሪዎች ናቸው፡፡ ከ2008 ዓ.ም በፊት የ12ኛ ክፍልን አጠናቅቀው ለመመዝገብ የሚመጡ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ሲስተሙ የማይፈቅድ በመሆኑ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የስራና ክህሎት ቢሮ አቅጣጫ እስኪሰጥ ድረስ በማንዋል (ወረቀት ላይ) እንዲመዘገቡ ተደርጓል፡፡ በሲስተም መመዝገብ ላልቻሉ ሰልጣኞች “ጉዳዩን የስራና ክህሎት ቢሮ እንዲያውቀው መደረጉንና ቢሮው በሚወስነው መሰረት እንደሚስተናገዱ” እንደተነገራቸው ገልጸዋል፡፡
የንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የሬጅስትራር ኃላፊ አቶ ሀብቶም አፅባሃ በኮሌጁ የ2018 የትምህርት ዘመን ምዝገባ በቴክኖሎጂ (ኢ-ስኩል) ስርዓት ተደግፎ እየተከናወነ ቢሆንም መመዝገብ የሚችሉት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን በ2008 ዓ.ም እና ከዚያ በኋላ የወሰዱት ብቻ መሆናቸው ችግር እየፈጠረባቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ከ2008 ዓ.ም በፊት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ አብዛኛው በእድሜ ከፍ ያሉና በማታው መርሃ ግብር ለመማር የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ከ2008 ዓ.ም በፊት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የወሰዱ 36 ትምህርት ፈላጊዎች በኮሌጁ ለመማር ቢያመለክቱም በሲስተሙ ምክንያት መመዝገብ ስላልተቻለ፣ የአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ ውሳኔ እንዲሰጥ ጥያቄ ማቅረባቸውንና እስከዚያው ድረስ ስማቸውንና የስልክ ቁጥራቸውን በመስጠት እንዲሄዱ ተደርጓል፡፡ “አንመዘግባችሁም አላልናቸውም፤ ስምና ስልክ ቁጥራቸውን ሰጥተው እንዲሄዱ ነው ያደረግናቸው፡፡ በማንዋል መዝግቡ ከተባልን እንመዘግባለን” ሲሉ ችግሩን በተመለከተ አቶ ሀብቶም አብራርተዋል፡፡
አቶ ሀብቶም፣ አሰልጣኞች የሰልጣኞችን ውጤት ወደ ሬጅስትራር የሚልኩት በኦንላይን ነው፡፡ በሲስተሙ መመዝገብ ያልቻሉ ሰዎች ቢመዘገቡ፣ ስማቸውን ኦንላይን ላይ ማግኘት አይቻልም፡፡ ባለፈው ዓመት በነበረው ምዝገባም በኢ-ስኩል እና በማንዋል የተመዘገቡ ሁለት ዓይነት ሰልጣኞች ነበሩ፡፡ ይህ ጉራማይሌ የሆነ አሰራር ለፋይል አያያዝና አስተዳደር የማይመች በመሆኑ፣ ከ2008 ዓ.ም ወደኋላ ያሉትንም ማስገባት እንዲቻል ሲስተሙ ላይ ማስተካከያ እንዲደረግ ጠይቀናል ብለዋል፡፡
በተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ከ2008 ዓ.ም በፊት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ፤ በዲፕሎማ፣ በድግሪና በሌላ ደረጃ ተመርቀው በኮሌጁ ለመማር የሚፈልጉ አመልካቾችን ለመመዝገብ ሲሰተም የማይቀበል ቢሆንም፤ በማንዋል (ወረቀት) በመመዝገብ እየተቀበሉ እንደሚገኙ በኮሌጁ የሬጅስትራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ስመኝ ሚዴቅሳ ለዝግጅት ክፍላችን አብራርተዋል፡፡
ቢሮው ምን ይላል?
አቶ ነጋ አርጋው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራና ክህሎት ቢሮ የውጤት ተኮር ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በ2018 የትምህርት ዘመን ተማሪዎች በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ለመመዝገብ የኢትዮጵያ ስራ ገበያ መረጃ አስተዳደር ስርዓት (Ethiopia Labor market Information system) በመታገዝ በስልክ ቁጥራቸው ከተመዘገቡ በኋላ ኮሌጅ ሬጅስትራር በመሄድ የሙያ ዝንባሌያቸውን በመምረጥ ፈተና ይወስዳሉ፡፡ በውጤታቸው መሰረትም የትኛው ዘርፍ ላይ ቢማሩ የተሻለ እንደሚሆን መረጃ (ምክረ ሀሳብ) ያገኛሉ፡፡
ከዚህ በመቀጠልም በከተማ አስተዳደሩ የለማ የተማሪዎች መመዝገቢያ ሲስተም (ኢ-ስኩል) ይመዘገባሉ፡፡ በዚህ ሂደት በመታገዝ በከተማዋ የሚገኙ 14 የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ምዝገባ እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ እስከአሁን ድረስም (መረጃውን እስካጠናቀርንበት እስከ 4/03/18 ዓ.ም ድረስ) ከ13 ሺህ በላይ ተማሪዎች ተመዝግበዋል፡፡ በከተማ ደረጃም በቀን፣ በማታ እንዲሁም በቅዳሜና እሁድ ፕሮግራም እስከ 19 ሺህ 500 ተማሪዎችን ለመቀበል ታቅዷል፡፡
ከምዝገባው ሂደት ጋር በተያያዘ በቴክኖሎጂ ተደግፎ የሚከናወነው (ኢ-ስኩል) ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን በተመለከተም አቶ ነጋ ሲመልሱ፣ ሲስተሙ ማስተካከያዎች የሚፈልጉ ነገሮች ቢኖሩም ባለው እየተሰራበት ነው። ሲስተሙ ከ2008 ዓ.ም በፊት የ12ኛ ክፍል ፈተና የወሰዱ ተማሪዎችን መቀበል አይችልም፡፡ ከዚህ በፊት የሆነ ቦታ ደረጃ ሁለት ወይም ሌላ ስልጠና ወስደውና የምስክር ወረቀት ይዘው የመጡት ተመዝጋቢዎችን ላያስተናግድ ይችላል። እነዚህን ሁለት መሰረታዊ ችግሮች እንዲስተካከሉ ሲስተሙን ላበለፀገው ድርጅት በደብዳቤ ጥያቄ መቅረቡንና በየጊዜው ክትትል እየተደረገበት እንደሚገኝ አቶ ነጋ ተናግረዋል፡፡
የዝግጅት ክፍላችን ባደረገው ቅኝት ከ2008 ዓ.ም በፊት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስደው፣ በሲስተም ችግር ምክንያት ምዝገባ ያላካሄደና የእናንተን ውሳኔ የሚጠብቅ ኮሌጅ አለ። ለዚህ ምላሻችሁ ምንድን ነው ያልናቸው አቶ ነጋ፣ “ሲስተሙ እስኪስተካከል ድረስ በማንዋል (ወረቀት) መመዝገብ የሚያስችል፣ ሲስተሙን ባለማው ድርጅት የተዘጋጀ የተመዝጋቢዎች መሰረታዊ መረጃ የያዘ ቅፅ (ቴምፕሌት) አለ፡፡ ይህንንም ለኮሌጆች ልከናል፡፡ አንዳንድ ተማሪዎች ጥያቄ ሲያቀርቡም ‘ተቀበሏቸው’ እያልን እያሳወቅን፤ በዚህ መሰረት ምዝገባ እያከናወኑ ይገኛሉ” ሲሉ መልሰዋል።የንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ላይ የተነሳውን ችግር በተመለከተም፤ “ተማሪዎችን እንዲቀበሉ ደውለንላቸዋል። በቴምፕሌት እንዲመዘግቧቸው ነግረናቸዋል፡፡” ብለዋል፡፡
የዝግጅት ክፍላችን ዳይሬክተሩ ያሉት ነገር ተፈጻሚ ስለመሆኑ ወደ ንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አቅንተው ከነበሩት ተመዝጋቢዎች የተወሰኑት ላይ ደውሎ ትክክል ስለመሆኑ ማረጋገጫ አግኝቷል፡፡
በስንታየሁ ምትኩ