መዲናዋ የአፈር ብክለትን ለመከላከል ምንእየሰራች ነው?

You are currently viewing መዲናዋ የአፈር ብክለትን ለመከላከል ምንእየሰራች ነው?

•   በአዲስ አበባ የሚከሰተው የአፈር ብክለት መንስኤ በዋነኛነት ኢንዱስትሪዎች መሆናቸው ተጠቁሟል

የአፈር ብክለት ከአካባቢ ብክለት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ “አፍንጫ ሲመታ አይን ያለቅሳል ለካ” እንደሚባለው የአንዱ መበከል ለሌላው ብክለት ምክንያት ይሆናል፡፡ ለምሳሌ፡- የአፈር ብክለት ከውሃ ብክለት ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ወንዞች ሲበከሉ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ አፈር ይበከላል፡፡ የተበከለ ወንዝ በመሬት ውስጥ ሰርጎ ሲገባ አፈር ይበክላል፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግ በዚህ ዕትማችን የአፈር ብክለት ምንነት፣ መንስኤዎቹ እና ተጽዕኖው እንዲሁም የአፈር ብክለትን በመከላከል እና በመጠበቅ ረገድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምን እየሰራ እንደሆነ እንቃኛለን፡፡

አቶ ሙላቱ ወሰን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የአካባቢ ብክለት ጥናት ባለሙያ ናቸው። እሳቸው አንደገለፁት፤ የአፈር ብክለት አፈር በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጥሮ ይዘቱን ማጣቱን የሚያመላክት ነው። የአፈር ብክለት በዋነኛነት በሰዎች፣ በእንስሳት እና ተክሎች አማካኝነት የሚከሰት ነው፡፡ ሰዎች ለተለያዩ አገልግሎቶች በፈሳሽ ወይም  በጠጣር መልክ የሚጠቀሟቸው ኬሚካሎች ከአፈር ጋር በሚዋሀዱበት ሰዓት የተፈጥሮ ይዘቱን ጠብቆ የቆየው ጤናማው አፈር ለብክለት ይዳረጋል፡፡ ተፈጥሯዊ ይዘቱን በማጣትም ጉዳት ያደርሳል፡፡ ይህ ሁኔታ ሲከሰት የአፈር ብክለት እንዳለ ይታመናል፡፡ 

የጥናት ባለሙያው አክለውም፤ የአፈር ብክለት ከአካባቢ ብክለት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የአካባቢ ብክለት እና ብክነት የሰው ልጅ ተደራራቢ እና ውስብስብ ችግሮች ውስጥ እንዲገባ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ቀዳሚው ነው፡፡ የአካባቢ ብክለት እና ብክነት የሚከሰተው በዋናነት የሰው ልጅ ተፈጥሮን ያለአግባብ በመጠቀም እንዲሁም እንክብካቤ ባለማድረግ ሲሆን፤ ሌላው በተፈጥሯዊ ምክንያት ነው፡፡ ብክነት ሲባል የአካባቢ ሃብቶች በተለይም የተፈጥሮ ሃብቶች በአግብቡ አለመያዝን የሚያመለክት ነው፡፡ ብክለት የሚባለው ደግሞ የአንድ አካባቢ አፈር፣ ውሃ፣ አየር፣ ድምፅ የመሳሰሉት ቁስ አካላዊ (ፊዚካላዊ) እና  ሥነ ህይወታዊ (ባዮሎጂካዊ) ይዘቶች ማጥፋት ወይም ማበላሸት ማለት ነው። የአካባቢ ብክለት የተፈጥሮን ወይም ሠው ሰራሽ ሀብቶችን በመበከል በሰው፣ በእንስሳት እና በሌሎች ህይወት ባላቸው ነገሮች ላይ ጉዳት ማድረስን ያጠቃልላል።

በመዲናችን አዲስ አበባ እንዲሁም በሀገራችን እየተስፋፉ ያሉ ኢንዱስትሪዎች፣ ሰፋፊ እርሻዎች በምርት ሂደት ውስጥ የሚጠቀሟቸው ግብአቶች እንዲሁም በምርቶች አያያዝ፣ አጠቃቀምና አወጋገድ ሥርዓት ማጣት ውስጥ የሚፈጠሩ ቆሻሻዎች ለአካባቢ በተለይም ለአፈር ብክለት ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ከኢንዱስትሪዎች የሚመነጭ ቆሻሻ ከምንጩ እንዲቀንስ ካልተደረገ ወይም በአግባቡ ካልተያዘ በአካባቢው የሚገኙ የውሃ አካላትን፣ አፈርንና ከባቢ አየርን በቀላሉ ሊበክል ይችላሉ፡፡

ሌላው ለአፈር ብክለት መንስኤ የሆነው ሰዎች በሚኖሩበት አካባቢ ቆሻሻን በአፈር ውስጥ በመወርወር እንዲሁም በአፈር ላይ ቆሻሻ ውሃን በማፍሰስ የሚያደርጉት የተሳሳተ ልማዳዊ ድርጊት ነው፡፡ ሰዎች በምርትና ምርታማነት ሂደት ውስጥ ተገቢ ያልሆነ የግብርና ግብአቶችን መጠቀም ለአፈር ብክለት ትልቅ ምክንያት ይሆናል፡፡ ለምሳሌ፡- የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ አጠቃቀም ላይ ከመጠን ያለፈ የናይትሮጅን፣ ፎስፎረስ እና ሌሎች ኬሚካሎች ወደ መሬት ሲገቡ አፈር ይበከላል፡፡ ከፍተኛ የእንስሳት ግጦሽ እና የእንስሳት እንቅስቃሴዎችም መሬት ላይ ያሉ ዕፅዋቶች እንዲራቆቱና እንዲጠፉ፣ አፈር እንዲሸረሸር እና ብክለት እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል፡፡

በሌላ በኩል፤ ለውበት የሚተከሉ ዛፎች ቅጠል በተገቢው ባለመወገድ ረግፈው ሲበሰብሱ የአፈር መጨናነቅን ያስከትላሉ፡፡ ይህም ሌሎች እፅዋት የሚያገኙትን የአየር፣ የውሃ እና አልሚ ምግቦች መጠን ሊቀንስ ይችላል። እነዚህ ሁሉ አፈሩን ሊያበላሹ ስለሚችሉ የተክሎችን እድገት አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡

የአፈር ብክለት በአዲስ አበባ

“በአዲስ አበባ ከተማ የአፈር ብክለቱ እስከምን ድረስ ነው? ከሌሎች አካባቢዎች በምን ይለያል?” ሲል የዝግጅት ክፍሉ ላነሳላቸው ጥያቄ የጥናት ባለሙያው አቶ ሙላቱ በሰጡት ምላሽ፤ “አዲስ አበባ ከተማ የበርካታ ኢንዱስትሪዎች መገኛ በመሆኗ በከተማዋ የሚከሰተው የአፈር ብክለት መንስኤ በዋነኛነት ኢንዱስትሪዎች ናቸው፡፡ አፈሩ እንዲበከል የሚያደርገው ዋና ምክንያትም በከተማዋ የሚገኙ አብዛኞቹ ፋብሪካዎች ፍሳሻቸውን ወደ ወንዝ ስለሚለቅቁ ነው። በተመሳሳይ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ያልተጣራ ፍሳሻቸውን ወደ ወንዝ ነው የሚለቅቁት፡፡ ግለሰቦችም የሚለቋቸው ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻዎች ሌላው የአፈር ብክለት መንስኤ ነው፡፡ ወንዝ ላይ ብክለት ተከሰተ ማለት ከአፈር ጋር ግንኙነት ስላለው አፈር ተበከለ ማለት ነው። የተበከለው የወንዝ ውሃ በመሬት ላይ ወይንም ወደመሬት ሰርጎ በመግባት አፈር እንዲበከል ያደርጋል” ብለዋል።  እነዚህ ከፋብሪካም ሆነ ከተቋማትና ግለሰቦች ወደ ወንዝ የሚለቀቁ መርዛማ ፈሳሽ ቆሻሻዎች ከአፈር ጋር ስለሚቀላቀሉ የአፈርን የተፈጥሮ ይዘት እንዲቀየር እንደሚያደርጉ አብራርተዋል፡፡

ችግሩን ለመከላከል ባለስልጣኑ ምን ሠራ?

የጥናት ባለሙያው አቶ ሙላቱ የአፈር ብክለትን እንዴት መከላከል እንደሚቻልና ችግሩን በመከላከል ረገድ ምን እየተሠራ እንደሆነ አያይዘው እንደገለጹት፤ በኢንዱስትሪዎች፣ በእርሻ ቦታ፣ በከተሞች፣ በቆሻሻ መጣያ ስፍራዎች ፍሳሽ ቆሻሻ ማከም፣ ከመኖሪያ የሚወጣን ፍሳሽ በተገቢው መንገድ ማስወገድ፣ ከሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ይልቅ የተፈጥሮ ማዳበሪያን መጠቀም እና የተበከለ ውሃን በማከም ጥቅም ላይ ማዋል ነው፡፡

ችግሩን በዘላቂነት በመከላከል ረገድ፤ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ይሰራል፡፡ በዘርፉ ለተሰማሩ ለሚመለከታቸው አፈርን ለሚጠቀሙ በተለይም የከተማ ግብርና ላይ ለሚሰሩ ባለሙያዎች እና አርሶ አደሮች ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተሰራ ነው፡፡ አፈር ሲበከል ሊያስከትል የሚችለውን የጤና ችግር ለማስገንዘብ እየተሰራ ነው፡፡ ግንዛቤ ከመፍጠር በተጨማሪ በደንብ ቁጥር 180/2017 ውሃው እንዳይበከል ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የቅጣት እርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡ በአፈር ውስጥ ያለውን የብክለት ደረጃ ለማወቅና “የጉዳት ደረጃው እስከምንድረስ ነው?” የሚለውን እንዲሁም ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል በተለያዩ አካላት ጥናቶች እየተከናወነ ነው፡፡ ጥናቱ በስፋት የሚደረገውም በመንግስት፣ በተቋማትና በግለሰቦች ቅንጅታዊ አሰራር ነው፡፡ በጥናቱም “አስጊ ነው ወይንስ ምን ላይ ይገኛል?” የሚለው ይታወቃል፡፡

በለይላ መሀመድ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review