ጉባኤውን የማስተናገድ ውሳኔው ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ ታሪካዊ መሆኑን ሊቀመንበሩ ገልጸው ይህም አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ እርምጃ ያላትን የማይናወጥ ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አማካኝነት እያሳየች ያለውን የአየር ንብረት የመሪነት ሚናም አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ የደን መልሶ ልማት እና አረንጓዴ ዐሻራን ጨምሮ ጠንካራ የአካባቢ ጥበቃ እርምጃዎችን እየወሰደች እንደምትገኝ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን በስኬት በማስተናገድ እምቅ አቅም እንዳላት አንስተው ከፍተኛ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ጉባኤዎችን ለማዘጋጀት ጠንካራ ተቋማዊ አቅም እና ልምድ አላት ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ እና የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ ጉባኤውን እንድታስተናግድ መመረጧ በዓለም አቀፍ ትብብር ያላትን ማዕከላዊ ሚና የበለጠ እንደሚያሳድገውም ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ(UNFCCC) እና አጋሮች ጋር በመሆን(ኮፕ 32) ሁሉን አካታችና ውጤታማ በማድረግ የአፍሪካን የአየር ንብረት የቅድሚያ ትኩረቶች የበለጠ ለማራመድና ዓለም አቀፍ አጋርነት ለማጠናከር በቅርበት እንደሚሰራ መግለጻቸውን ህብረቱን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።
በብራዚል ቤለም እየተካሄደ የሚገኘው 32ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባኤ(ኮፕ 30) ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2027 የሚከናወነውን ኮፕ 32 እንድታስተናግድ ተመርጣለች።
የአፍሪካ ሀገራት ለኢትዮጵያ የኮፕ 32 የማስተናገድ ፍላጎት ሙሉ ድጋፋቸውን መስጠታቸው ይታወሳል።