በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ለዘመናት የዘለቀው ግጭት መነሻ ከድንበር ውዝግብና ከባህር በር ፍላጎት የተሻገረ በመሆኑ የኢትዮጵያን የሰላምና የልማት ፍላጎት በየጊዜው የሚገዳደር ሆኗል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ገለጹ።
“ሆርን ሪቪው” የተባለው ቲንክ ታንክ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የፖሊሲ ፎረም አካሂዷል።
በፎረሙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡና አጋር አካላትን ጨምሮ ፖሊሲ አውጪዎችና ምሁራን የታደሙ ሲሆን፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ(ዶ/ር) በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም፤ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ግጭትና አለመረጋጋት ዋነኛ መገለጫ እየሆነ መጥቷል በሚል ከሁሉም የሚዲያ አማራጮች መስማት የተለመደ ነው።
ቀጣናው ሰፊ የሚታረስ መሬት፣ የውሃ ሀብት፣ እምቅ የተፈጥሮ ማዕድንና ጠንካራ ሰራተኛ ሕዝብ ያለው መሆኑን አመልክተው፤ በአካባቢው በሚፈጠሩ ግጭቶች ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ አዳጋች እንዳደረገውም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ይህን ለረጅም ጊዜ የልማት፣ የሰላምና የደህንነት ስጋት የሆነውን ቀጣና ለመቀየር በመሰረተ ልማትና በኢኮኖሚ ትስስር እንዲፈጠር ጥረቶች እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቅድሚያ ለጎረቤት የሚሰጥ፣ ከሁሉም ጋር በሰላማዊና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ አብሮ የመስራት ዓላማ መያዙን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር በሰላማዊና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ አብሮ የማደግ ፍላጎቷን በመሰረተ ልማትና በኤሌክትሪክ ሃይል ትስስር በተግባር ማሳየቷንም አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት እያደገ ከመጣው የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር አኳያ እንዲሁም እየተመዘገበ ያለውን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠል የባህር በር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ቀደም ባሉት ዓመታት የባህር በር የነበራት ሀገር ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንድታጣ መደረጉን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ አንድ ሀገር እንደነበሩ ያስታወሱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ በወቅቱ ኢትዮጵያን የመሩ መንግስታት ሃላፊነት በጎደለው መልኩ ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠልና ከባህር እንድትነጠል ማድረጋቸውን አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ለዘመናት የዘለቀው ግጭት መነሻ ከድንበር ውዝግብና ከባህር በር ፍላጎት የተሻገረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የኢትዮጵያን የሰላምና የልማት ፍላጎት በየጊዜው የሚገዳደር መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደት ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረገች መሆኑን ያብራሩት ሚኒስትሩ፤ ሁሉም ሀገሮች ለዚህ ሊተባበሩ ይገባል ብለዋል።
የውጭ ጣልቃ ገብነትን መከላከልና የንግድና ኢንቨሰትመንት ግንኙነትን ማሳደግ ለቀጣናዊ ኢኮኖሚ ውህደት መሳካት ወሳኝ መሆኑንም ነው ያነሱት።
እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ዘላቂ ልማትን ለማምጣት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፉን ማጠናከር አለበት።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ከሰሩ ለሌሎች ሀገሮች ምሳሌ የሚሆን ትብብር መፍጠር እንደሚችሉ መናገራቸዉን ተዘግቧል።