ፅዱና ምቹ የመኖሪያ አካባቢን መፈጠር የከተሜነት መገለጫ ከሚባሉ መለኪያዎች ውስጥ አንዱ በመሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች የመኖሪ አካባቢያቸውን ፅዱና ጤናማ የማድረግ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ አሳሰቡ፡፡
‹‹ህዳር ሲፀዳ ለአካባቢያችን ጤና›› በሚል መሪ ሃሳብ የፅዳት ንቅናቄ ማስጀመሪያ ዘመቻ በየካ ክፍለ ከተማ በወረዳ ስድስት ተካሂዷል።
ህዳር ሲፀዳ ለአካባቢያችን ጤና በሚል መሪ ሃሳብ የተካሄደውን ንቅናቄው ያስጀመሩት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ “ህዳር ሲታጠን” በሚል በልማዳዊ እሳቤ ሲተገበር የቆየውን ባህላዊ የቆሻሻ አወጋገድ ስርአት ‘ህዳር ሲጸዳ” በሚል በዘመናዊ የቆሻሻ አስተዳደር ስርአት መተካት ማቻሉን አብራርተዋል፡፡
ምቹ የመኖሪያ አካባቢን መፈጠር እና የሰለጠነ ማህበረስብን መገንባት የከተሜነት መገለጫ ከሚባሉት ውሰጥ አንዱ ስለመሆኑም ኢንጂነር ወንድሙ ተናግረዋል፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎች የመኖሪ አካባቢያቸውን ፅዱና ጤናማ የማድረግ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ጥሪ አቅርበዋል።
የካ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍጹም ሃይሌ የኮሪደር ልማት ስራው ከተማዋ ውብ እና ንጹህ እንድትሆን ማስቻሉን አስታዉስው የከተሜነት መገለጫ የሆነው የጽዳት መርሃግብር በትምህርት ቤቶችና በማህበረሰቡ ላይ በተሰራው ስራ ግንዛቤው እያደገ ስለመምጣቱ ተናገረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፅዳት አስተዳደር ኢጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ ደሲሳ በበኩላቸው አካባቢያችንን በማፅዳት የዜግነት ግዴታችንን በመወጣት ህዳርን በንፅህና ልናሳልፍ ይገባል፤ በአግባቡ የተያዘ ደረቅ ቆሻሻ ሀብት ነው፤ ንፁህ አካባቢ ሲፈጠርም የራሳችንም የአካባቢያችንም ጤና የተጠበቀ ይሆናል ብለዋል።
የጽዳት መርሃብሩ ተሳታፊ የነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች በጽዳት ዘመቻ ሁሉም ማህበረሰብ መሳተፍ እንዳለበት ለኤ ኤም ኤን ገልፀዋል።
በመሀመድኑር አሊ