እራስን የማግኘት አብዮት ላይ ያተኮረው “ምልዓት” የተሰኘው መፅሐፍ ተመረቀ

You are currently viewing እራስን የማግኘት አብዮት ላይ ያተኮረው “ምልዓት” የተሰኘው መፅሐፍ ተመረቀ

AMN- ህዳር 6/2018 ዓ.ም

እራስን የማግኘት አብዮት ላይ ትኩረት ያደረገው “ምልዓት” የተሰኘው መፅሐፍ ተመርቋል።

መፅሐፉ የደራሲው አለማየሁ አረዳ (ዶ/ር) ቤተሰቦች፣ ጓደኞቻቸው እና መፅሐፍ አንባቢ ቤተሰቦች በተገኙበት በአብርሆት ቤተ-መፀሐፍት ተመርቋል።

በምረቃ መርሐ-ግብሩ መፅሐፉ ለሁሉም ህብረተሰብ በተለይም ወጣቱን ማዕከል ያደረገ መሆኑን የገለጹት የመፅሐፉ ደራሲ አለማየሁ አረዳ (ዶ/ር)፣ ወጣቱ ምክንያታዊ እና በነገሮች ላይ የራሱ ምልከታ እንዲኖረው ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

መፅሐፉ ሰው የመሆን ሰዋሰውን በግልፅ ለማሳየት እና እራስን ለማወቅ አቅጣጫ አመላካች እንዲሆን ታስቦ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።

ይህም ወጣቱ ፍቅርን፣ እውቀትን፣ ነፃነትን እና እውነትን አስተባብሮ በመረዳት እራሱን እንዲፈልግ አቅጣጫ አመላካች መሆኑንም አስረድተዋል።

ለዚህም “ፍቅር እና እውቀት ሲተቃቀፉ ማንነት በልዩነት ውስጥ ክብርን ሲያይ ነፃነት ከእውነት ጋር ጎን ለጎን ሲጓዝ አዲሱ አይነት ሰው ብቅ ይላል” በማለት በመፅሐፋቸው መግለፃቸውን ጠቅሰዋል።

“ምልዓት” በጥቅሉ አዲስ አብዮት ሲሆን፣ ይህም ሰውን እረስተው ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይን ብቻ አንግበው እንደሚካሄዱት አብዮቶች ሳይሆን፣ እራስን የማግኘት አብዮት መሆኑን ገልጸዋል።

በመርሐ-ግብሩ መምህራን፣ ጋዜጠኞች እና የስነ-ልቦና ባለሙያዎች ስለ መፅሐፉ ይዘት እና ስለ ደራሲው እይታ የተለያዩ ምስክርነቶችን ሰጥተዋል።

ደራሲ አለማየሁ አረዳ (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም “ምሁሩ” እና “የሰጎን ፖለቲካ” የተሰኙ መፅሐፍቶችን ለአንባቢያን ማበርከታቸው ይታወሳል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review