በኢትዮጵያ እየተከናወነ የሚገኘው የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ መንግሥት ወቅቱን የጠበቀና ጥራት ያለው ውሳኔ እንዲሰጥ እንደሚያስችል የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ(ዶ/ር) ገለጹ።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ አገልግሎቱ ከ2016 ዓ.ም እስከ 2018 ዓ.ም የስታቲስቲክስ ልማት ፕሮግራም ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
ለፖሊሲ አውጪዎች፣ ለተመራማሪዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎችን በመሰብሰብ ተደራሽ እያደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሥነ ህዝብና ጤና ጥናት፤ የኢትዮጵያ የግብርና ቆጠራ፣ ብሔራዊ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናትና የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ የትኩረት ዘርፎቹ እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሥነ ህዝብና ጤና ጥናት መጠናቀቁን ገልጸው፤ የኢትዮጵያ የግብርና ቆጠራ እና ብሔራዊ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት በመገባደድ ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡
የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ከ20 ዓመት በፊት ተከናውኖ እንደነበር አስታውሰው፤ የ2018 ዓ.ም ቆጠራ ጥቅምት 7 ቀን 2018 ዓ.ም መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
ቆጠራው 19 የሚሆኑ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ምድብ ስያሜዎችን በመከተል እንደሚከናወን ገልጸው፤ በመላ ሀገሪቱ ያሉ ጥቃቅንና አነስተኛ፣ መካከለኛ፣ ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች እና የንግድ ባህሪ ባላቸው ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ ያተኩራል ብለዋል፡፡
የኢኮኖሚ ተቋማት ቆጠራ በሁሉም ከተሞች ቤት ለቤት በመዞርና በገጠር ናሙና በመውሰድ እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡
የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ የመንግስት ውሳኔ ሰጪ አካላት ጥራት ያለውና መረጃን መሰረት ያደረገ ወቅቱን የጠበቀ ውሳኔ እንዲሰጡ ያስችላል ብለዋል፡፡
ፍትሃዊና ትክክለኛ ውሳኔ በመስጠት ሀገራዊው ዕድገት ከየት ወደ የት እየሄደ እንዳለ ለማወቅ እንደሚረዳም ገልጸዋል፡፡
በእያንዳንዱ ክፍለ ኢኮኖሚ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ምን ያህል እንደሆነ መለየት እንደሚያስችል ገልጸው፤ ይህም ኢኮኖሚያዊ ትንተናና ግምገማ ለማካሄድ ያግዛል ብለዋል፡፡
የሴቶችና አካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ በመለየት በገጠርም ሆነ በከተማ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልና ተደራሽነት ለማረጋገጥ እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡
በ2019 የኢትዮጵያ አጠቃላይ ምርት(GDP) ግመታ ላይ ክለሳ እና የኢትዮጵያ የድህነት ምጣኔ እንደሚለካ በመጥቀስ፤ ቆጠራው ለዚህ መነሻ ይሆናል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት መዋቅራዊ ሽግግር ምን ደረጃ ላይ እንዳለ መረጃ እንደሚሰጥም ተናግረዋል፡፡
አዲስ የመረጃ ቋት በማበልፀግ መንግስት የፖሊሲና እቅድ መነሻ በማድረግ የፖሊሲ ውጤታማነትን ለመገምገም አቅም እንደሚሆንም አንስተዋል፡፡