መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ህዝቡ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለውን ቅሬታ በዘላቂነት ይፈታል

You are currently viewing መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ህዝቡ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለውን ቅሬታ በዘላቂነት ይፈታል

AMN- ህዳር 6/2018 ዓ.ም

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የደሴ ከተማን መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት አስጀምረዋል፡፡

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ህዝቡ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለውን ቅሬታ በዘላቂነት እንደሚፈታ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የደሴ ከተማን መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት ባስጀመሩበት ወቅት ገልጸዋል፡፡

ደሴ ከተማ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ዘመን ተሻጋሪ ገድል የጻፈች፣ የሰለጠነ ማህበረሰብ የገነባች፣ የዘመናዊ መገለጫ ከተማ መሆኗንም ገልጸዋል፡፡

ህዝቡ አስተዋይ፣ ለፍትህ የቆመ፣ በውይይት የሚያምን፣ የሰላም አምባሳደር የልማት አርበኛ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የወሎ ምድር ለኢትዮጵያዊነት የመደመር ቅኝት ማሳያ፣ ድንቅ እሴት እንደ ቦርከና ወንዝ ሞልቶ የሚፈስበት የአብሮነት እና የመዋደድ ተምሳሌት መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ወሎ የጥበብ መፍለቂያና የዕውቀት ማዕድ መሆኗን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የወሎዋ ዕምብርት ደሴ ከተማ አሁን በከፍተኛ የልማተ እንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡

የደሴ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት በከተማዋ የተጀመረውን የልማት ጉዞ ለማሳለጥ የጎላ አበርክቶ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢኒሼቲቭ የሆነው መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት በተለያዩ አካባቢዎች በማንዋል ሲሰጥ የቆየውን የመንግሥት አገልግሎት በአንድ ማዕከል ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

በመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት የተገልጋዮችን ጊዜና ጉልበት በመቆጠብ በህዝብና መንግሥት መካከል ያለውን ጥብቅ ቁርኝት ወደ ተሻለ ደረጃ እንደሚያሳድግ ገልጸዋል፡፡

ብልሹ አሰራርን በማስወገድ ዘመኑን የዋጀና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል ገልጸው፣ በደሴ ከተማ የተሰራው ማዕከል የህዝቡን የረጅም ጊዜ የፈጣን አገልግሎት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በለውጡ መንግሥት ደሴ የብልፅግና ብርሃን ወጋገን ፈንጥቃለች፣ ለነዋሪዎቿ ምቹ የበለፀገች እና የተዋበች ከተማ መሆን የሚያስችላትን የተስፋ ጎዳናም ጀምራለች ብለዋል፡፡

የመጀመሪያው ምዕራፍ የደሴ የኮሪደር ልማት የከተማዋን ውበት እየገለጠ መሆኑን ጠቅሰው ለተሻለ አፈጻጸም ህዝቡና አመራሩ ተጋግዞ መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

ሰላምና ልማት ተመጋጋቢ መሆናቸውን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የተጀመረው ልማት ከግብ እንዲደርስ ህዝቡ የሰላም ዘብነቱን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review